ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዓለም ላይ ትልቅ ገዳይ የሆነውን የኤድስ በሽታን የሚያስከትለው የኤችአይቪ ቫይረስን ለመከላከል ይረዳል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበት የኘበረው የሙከራ ክትባት ሳይሳካ ቀረ።
አስከፊውን የቫይረሱን ስርጭት ይገታል በሚል በሕክምና ባለሙያዎች ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሙከራን እውን ለሚድረግ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከአምስት ሺህ በሚልቁ ሰዎች ላይ የክትባቱን ሙከራ ያደረገው፣ ብሔራዊ የጤና ተቋም ፤ ክትባቱ ኤችአይቪን መከላከል እንዳልቻለ ስለደረሰበት ሙከራው እንዲቆም ማድረጉን በይፋ አረጋግጧል።
በሥራው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተገኘው ውጤት በጣም ማዘናቸውን ጠቁመው፤ ነገር ግን ኤችአይቪን የሚከላከል ክትባት የማፈላለጉ ጥናት በዚህ ሳይቆም ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ክትባቱ ታይላንድ ውስጥ በተደረገ ሙከራ ሰዎችን ከበሽታው ለመከላከል የሚያስችል አቅምን ይፈጥራል ተብለው ከታሰቡት የክትባት አይነቶች መካከል አንዱ ነበር።
በዓለም ላይ በርካታ የተለያዩ አይነት የኤችአይቪ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ፤ ይህ ክትባት በተለይ ኤችአይቪ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ካለባቸው አገሮች አንዷ በሆነችው በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በስፋት ለሚገኘው የቫይረሱ ዝርያ ታስቦ የተዘጋጀ እንደነበር ታውቋል።
ክትባቱ በሙከራ ላይ ሳለ እንደታሰበው በመሥራት በሌሎች የዓለም አካባቢ ላሉት የቫይረሱ አይነቶች የሚሆኑ ክትባቶችን ለማዘጋጀት ያግዛል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ቆይቷል። ለክትባቱ ሙከራ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ተዘጋጅተው ለተወሰኑት ለበሽታው ይሆናል የተባለው ክትባትና ለሌሎቹ ደግሞ ምንም ሳይሰጣቸው ሙከራ ሲደረግ፤ በተገኘው ውጤት ግን ክትባቱ ከተሰጣቸው መካከል 129ኙ በሽታው ሲገኝባቸው፤ ካልተሰጣቸው ውስጥ ደግሞ 123ቱ በበሽታው ተይዘዋል።
የተገኘው ውጤት በምርምሩ ላይ የተሰማሩትን ባለሙያዎች ተስፋ አስቆርጧል። ነገር ግን በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት መቀጠል እንዳለበት ያምናሉ።
ቀደም ሲል በበሽታው ከመያዝ የሚከላከል ውጤታማ የሆነ ሕክምና ያለ ሲሆን ነገር ግን ከክትባት በተለየ መድኃኒቱን በመደበኝነት በየቀኑ መወሰድን ያስፈልጋል። ከዚህ በተለየ በሽታውን ለመከላከል እንደዋነኛ ዘዴ የሚመከረው በተገቢው ሁኔታ ኮንዶም መጠቀም ወይም ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መታቀብ ቀዳሚው ሆኗል።