ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሀዋሳ ከተማ 29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ከተሸከርካሪው ጋር መያዙን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል ፡፡
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ ኮለኔል ሮዳሞ ኪአ ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሓላፊ ኮማንደር ኢዮብ አቤቶ በጉዳዮ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል ።
ትላንት ምሽት 5 ሠዓት አካባቢ አይሱዙ ኤፍ.ኤስ.አር ተሸከርካሪ 29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመኪናው ከፋብሪካ ውጭ በተሠራ በቀላሉ የማይገኝ ሚስጥራዊ ቦታ ተደብቆ ሲጓዝ በቁጥጥር ስር መዋሉን መግለጫው ያስረዳል።
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዙ የነበሩት የመኪናው አሽከርካሪ፣ የህገ-ወጥ ጦር መሳሪያው ባለቤት እና የመኪናው ረዳት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መረጃው ከሳምንት በፊት አስቀድሞ በደረሰ ጥቆማ የታወቀ መሆኑ ሲሆን፤ ብቃት ያላቸውን የፖሊስ አመራሮች በመመደብ ጉዳዩ በሚስጥር ሲጣራ ቆይቶ ትላንት ምሽት መያዙን ሓላፊዎቹ አብራርተዋል።
የተያዘው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያው ከየት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ እና ለምን ዓላማ ሊውል እንደተፈለገ ጭምር መረጃዎች መኖራቸው እንደታወቀና ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ይፋ ተደርጓል።