ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግተው የሚገኙ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው እገታ በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ካገጠሙ ችግሮች ውስጥ አንዱ መሆኑንምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
“በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ የተጨበጠ ውጤት ላይ ለማድረስ መንግሥት ሙሉ ኃይሉን አሰባስቦ እየተረባረበ” እንገኛለን በማለትም መንግሥት በጉዳዮ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰባት ቤት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በእንጅባራ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ላይ ነው እንዲህ ሲሉ የተደመጡት። “መንግሥትን በማመን ከወላጆቻቸው ተነጥለው በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች እገታ በወቅቱ እንደ አገር ከገጠሙን ፈተናዎች መካከል አንዱ ወቅታዊ ፈተና ነው” ሲሉም የችግሩን ጥልቀት አመላክተዋል።
ተማሪዎቹ ከታገቱበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ መሆኑን የጠቀሱት ም/ጠ/ሚኒስትሩ ተጨባጭ ውጤት ላይ አለመደረሱና የተማሪዎቹ እገታ የወሰደው ረጅም ጊዜ የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦችንና ሕዝቡን ባልተቋጨ ጭንቀትና ባልተፈታ ሐዘን ውስጥ እንዲቆዩ አስገድዷቸዋል ብለዋል ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ችግሩ ውስብስብ መሆኑን ያመላከቱት ደመቀ መኮንንበቅርቡ ከታጋች ቤተሰቦች ጋር ፊት ለፊት በተደረገ ውይይት በተለያዩ ወገኖች ያልተጣሩና ተለዋዋጭ መረጃዎች መሰራጨታቸው የታጋች ቤተሰቦችን ስጋትና ጭንቀት እጅግ መራር እንዳደረገው ለመረዳት እንደተቻለም አስረድተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተማሪዎቹና በወላጆቻቸው ላይ ባጋጠመው አሳዛኝ ክስተት እንደወላጅ “ከልባችን አዝነናል” ሲሉም ስሜታቸውን በሐዘን ድባብ ገልጸዋል። እገታው መንግሥት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅና ችግር ሲያጋጥምም ፈጥኖ የመፍታት አቅሙን ማጠናከር እንዲሁም ድክመቶችን ማረም እንዳለበት በከፍተኛ ሁኔታ ያመላከተ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
• ተለቀዋል የተባሉት ታጋቾች የት ናቸው?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ዕገታው ያጋጠመበት አካባቢ “የሰላምና የጸጥታ ችግር የሚስተዋልበት በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ የችግሩ ሰለባ ሆነው ቆይተዋል” ሲሉ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የነበረ መሆኑን አመልከተዋል።
በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደተናገሩት በዩኒቨርስቲዎች የተረጋጋ ድባብ እንዳይሰፍን ፍላጎት ባላቸው አካላት ከዚህ በከፋ ደረጃ ጉዳት እንዳይደርስና አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ “በየደረጃው የምንገኝ አካላት በተግባር የመፍትሄው አካል ሆኖ መገኘት የሚጠይቀን ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ብለዋል።
ከሰሞኑ ስለታገቱ ተማሪዎች ለመጠየቅ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተካሄዱትን ሰልፎችን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሰልፎቹ በሰላማዊ ሁኔታ መካሄዳቸው የሚያስመሰግን ነው” ሲሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላትን በተመለከተም “ስህተትን ላለመድገም በማረም፤ እንዲሁም ተጨባጭ ሁኔታ ያለፈቀደውን በግልጽ በማሳወቅ ሁሉም የመፍትሄ አካል መሆን ኃላፊነትም ግዴታችንም ነው” ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን