መብራት ኃይል በ58 ሚሊዮን ዶላር ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ አስመረቀ

መብራት ኃይል በ58 ሚሊዮን ዶላር ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ አስመረቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በተለይም በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ የመብራት መቆራረጥ የሚስተዋልበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ58 ሚሊየን ዶላር ወጪ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ ፕሮጀክት ማስመረቁ ተነገረ።

ኢ.አር.ፒ ወይም ኢንተርፕራይዝ ሪሶስር ፕላኒንግ የተሰኘው ይህ መተግበሪያ የተቋሙን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከማሳደግ ባሻገር ለተገልጋዮች ቀልጣፋ፣ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት መስጠት ያስችላል እየተባለለት ነው።ከመተግበሪያው በተጨማሪ ድርጅቱ የተጓዳኝ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ፕሮጀክትም በተያያዥነት እንዳስመረቀ ተሰምቷል።

የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ እና ሌሎች የሥራ ሓላፊዎች በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፥ ፕሮጀክቱ ፍትሀዊ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ግልፅ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የኃይል ብክነትን ለመቀነስና የተቋሙንም ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

ተቋሙ ራሱን ለማዘመን በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እየሠራ ሲሆን ፤ በዘርፉ ልምድ ካለው ከህንዱ ቴክ ማሂንድራ ኩባንያ ጋር በ2008 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ላለፉት አራት ዓመታት ሲተገበር መቆየቱና ውጤታማነቱ መረጋገጡ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

አዲሱና ዘመናዊው መተግበሪያ ለዕለታዊ ተግባር የሚያስፈልግ ሀብትና ግብዓትን ማቀናጀት፣ የመረጃ ፍሰትን ማሳለጥ፣ መረጃዎችን በአንድ ቋት ፈጥሮ ወጥነት ባለው መልኩ ማቀናጀት የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር ፤ ለማምረቻ፣ ለግዥና አቅርቦት ስርጭት፣ ለሂሳብ አያያዝ፣ ለግብይት፣ ለደንበኞች መስተንግዶ፣ ለሰው ኃይል ቁጥጥርና ሌሎችም ዘርፎችም አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።

ለተገልጋዮች የተቀናጀ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና የተጠቃለለና የተደራጀ ሪፖርት ለማግኘት እንደሚያግዝም ተጠቁሟል። የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ የሥራ አመራር ቦርዱ መንግሥት ለኃይሉ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራም ለተጠቃሚዎች የኃይል ውስንነት መኖሩ የቅሬታና መልካም አስተዳደር ምንጭ እንደሆነ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ራሱን አዘምኖ ውጤታማ እንዲሆን መፍትሄዎችን ማስቀመጡን ጠቅሰው፤ አሠራሩን ያልተማከለ ማድረግ፣ የጥገናና መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለሦስተኛ ወገን መስጠትና የውስጥ አሠራሩን በቴክኖሎጂ መቀየር  ዋነኛ ትኩረቱ መሆናቸውን ሓላፊው በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY