ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በቻይና ውሃን ከተማ ያሉ ዮንቨርስቲዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መንግሥት ከጭንቀታችን ይገላግለን፣ ወደ አገር ቤትም ይመልሰን ሲሉ ተማጸኑ::
በውሃን ዮንቨርስቲ ከሦስት መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ያሉ ሲሆን በሁቤይ ግዛት ውስጥ ከተሞች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስን ከቀን ቀን መስፋፋት ተከትሎ በስጋት ውስጥ ይገኛሉ::
በተለያዮ ዮንቨርስቲዎች ውስጥ የአገሪቱ መንግሥት ለተማሪዎች ምግብ፣ ውሃና ሌሎች ቁሳቁሶችን እያቀረበ ቢሆንም ኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች በከፍተኛ ጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ነው የተሰማው:: ተማሪዎቹ አሁን ላይ ወደ አገራቸው መመለስ ቢፈልጉም ከውሃን ከተማ መውጣትም ሆነ መግባት መከልከሉ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሮባቸዋል::
በሆዋጆንግ ዮንቨርስቲ ኦፍ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ በሶሻል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት የዶክትሬት ተማሪ የሆነችውና በቻይና ውሃን ከተማ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት ዘሃራ አብዱልሃጅድ ተማሪው ከእንቅስቃሴ መገደቡ በራሱ ተጨማሪ ጭንቀት የፈጠረበት መሆኑን ለቢቢሲ ተናግራለች::
በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ግፊት ተከትሎ ኅብረቱ ተማሪዎችን መንግሥት እንዲያስወጣቸው ጥያቄያቸውን ለኤምባሲ ማቅረባቸውን የተማሪዎቹ ኅብረት ፕሬዝዳንት ጠቁማለች::
ተማሪዎች ከቤተሰባቸው በሚመጣው ግፊትና በሚያዮት ስጋት “ኳረንታይ መደረግ ካለብን እንደረግ፤ ወደ ቤተሰባችን መቀላቀል ይሻለናል” በሚል በኅብረታቸው በኩል ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸው:: ኤምባሲው “ታገሱን አወጣጡ የራሱ የሆነ ሂደት አለው” ሲል ከውጭ ጉዳይ መ/ቤት ጋር በጉዳዮ ላይ በጣምራ እየሠራ መሆኑን በተወካዮቹ በኩል ምላሽ ሰጥቶበታል::