ሁለቱ ሰማእታት በታላቅ ክብር ግብዓተ መሬታቸው ተፈጸመ

ሁለቱ ሰማእታት በታላቅ ክብር ግብዓተ መሬታቸው ተፈጸመ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ማክሰኞ እለት እኩለ ሌሊት ላይ የቤተ ክርስቲያን ቦታን ሊያፈርሱ በመጡ የፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የተገደሉት ሁለቱ የአዲስ አበባ የ24 ቀበሌ ሰማእቶች በታላቅ ክብር ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል::

 ድንቁ ድንበሩ እና ሚካኤል ሚሊዮን የተባሉት እነዚህ ሁለት ሰማእት ትናንት የተከበረውን የመድኃኒዓለም ንግስ በማስመልከት ምእመናንና ካህናትን በክብረ በዓሉ ላይ ለመመገብ ከቀን እስከ ኤኩለ ሌሊት፣ ታቦተ ሕጉና ቤተክርስቲያኑ እንዲያርፍ በተከለለበት የማምለኪያ ቅፅር ግቢ ውስጥ በሥራ በተጠመዱበት ወቅት ነበር ሕይወታቸውን ያጡት። 

በታከለ ኡማ ቀጥተኛ ትእዛዝ ሥር መደበኛ ሥራውን የሚያከናውነው የቦሌ ክፍለ ከተማ ለአስር ዓመታት ሕጋዊ  የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኝ ሲጠይቅ የኖረውን የጠቅላይ ቤተ ክህነትን ጥያቄ ሳይመልስ፤ በውድቅት ሌሊት ድፍረት የተሞላበት እርምጃ መውሰዱ ምእመኑን በከፍተኛ ሁኔታ አበሳጭቷል። 

የእምነት ቦታውን አናስነካም በሚል ሰማእት የሆኑት  ሁለት ሰዎች አስከሬን  ለምርመራ ተወስዶ ከነበረበት ሆስፒታል ወደ መኖሪያ ቤታቸው ከተወሰደ በኋላ በልዮ ክብር ታጅቦ የፍትሀትና የሽኝት ፕሮግራም በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ተደርጎለታል::

የሰማእታቱ የሣህለ ማርያም እና ኃይለ ሚካኤል ጸሎተ ፍትሐት በቦሌ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁአን አበዉ፣ ሊቃነ ጳጳሣትና ምእመናን በተገኙበት በሕገ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

ከፍትሀቱ በኋላ የሁለቱ ሰማእታት አስከሬን በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እና በክርስቲያኒያዊ ዝማሬዎችና በብዙ ሺኅ ምእመናን ታጅቦ  ወደ ገርጂ ቅዱስ ገብርዔል ቤተ ክርስቲያን ተሸኝቶ በዚሁ ቤተክርስቲያን ግብአተ መሬቱ እንዲፈጸም ተደርጓል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰማእታቱ አስከሬን ከቦሌ መድኃኒ ዓለም  ወደ ገርጂ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በምእመናን ታጅቦ በሚሸኝበት ወቅት አዲሱ ስታዲየም ከሚገነባበት ሥፍራ ፖሊሶች ከምእመናን ጋር ግጭት ለመፍጠርና ኹከት ለመቀስቀስ ሲሞክሩ ተስተውሏል። 

ፌደራል ፖሊስና አዲስ አበባ ፖሊስ  አባላት ከአንድ ቀን በፊት የፈጸሙት ነውረኛ ተግባር ሳይጸጽታቸው “አንመካም በጉልበታችን፣ እግዚአብሔር ነው የእኛ ኃይላችን” በማለት ሲዘምሩ የነበሩ ወጣቶችን የያዙትን ሰንደቅ ዓላማ ለመንጠቅ መሞከራቸውን ተከትሎ ነው ውዝግቡ የተፈጠረው። 

ከስታዲየሙ  ግቢ ውስጥ ተደብቀው ቆይተው ድንገት ብቅ ያሉት ፖሊሶች የምእመኑ አንድነት እና ያለ ፍርሃት መታገል አስደንግጧቸው አንድም ሰንደቅ አላማ ሳይነጥቁ ወደ መጡበት ተመልሰዋል። 

LEAVE A REPLY