ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለ33ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የአፍሪካ አገራት እና መንግሥታት መሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።
እስከ ከሰዓት በኋላ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት አስማኤል ኦማር ጌሌህ መግባታቸው ሲታወቅ ማምሻውን የተለያዮ አገራት መሪዎች አ/አ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደረሱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ተጋባዥ ከሆኑት መሪዎች ውስጥም የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አቀባበል ሳይደረግላቸዋል።
33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን እሁድ እና ሰኞ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ከዚያ ቀደም ብሎ የኅብረቱ የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ጉባኤም ትናንት እና ዛሬ ተካሂዷል። ጉባኤው “ግጭትና ጦርነትን በማስቆም ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት”በሚል መሪ ቃል ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።
ለጉባኤው ከኅብረቱ አባል አገራት መሪዎች በተጨማሪ የተመድ ዋና ጸሐፊ እና የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም ዐቀፋዊ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ሓላፊዎች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ ነው የተባለው።