ፕ/ንት ኢሳያስ አፈወርቂ መቀሌ የመሸገው ህወሓትን ከሰሱ

ፕ/ንት ኢሳያስ አፈወርቂ መቀሌ የመሸገው ህወሓትን ከሰሱ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ከሚሰጡት ቃለ ምልልስ አንዱ በሆነውና የመጀመሪያው ክፍል ትናንት አርብ ምሽት በሰጡት ማብራሪያ ላይ፤ በተለይ ኤርትራ ከኢትዮጵያና ሌሎች ጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አስመልክተው ሰፋ ያለ ማብራሪያ  ሰጡ።

ኢሳያስ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መበላሸት ምክንያት ስለሆነው የድንበር ጥያቄ  ላይ በባድመ ጉዳይ ስምምነቱ እንዳይፈጸም ህወሓት ትልቅ እንቅፋት መሆኑን አጋልጠዋል።” በወረራ የተያዘው የኤርትራ ሉዓላዊ መሬት ያልተመለሰው ህወሓት እምቢ በማለቱ ነው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ መቀሌ የመሸገውን ህወሓት ከሰዋል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የተደረገው የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት እልባት ይሰጣል የተባለውን የድንበር ጉዳይ አስመልክቶ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ  አፈወርቂ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ህወሓት በድንበሩ ጉዳይ የወሰደውን አቋም አጣጥለዋል።

“ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የተናገሩት የስምምነት ሃሳብ ሳይተገበር፣ የባድመ የድንበር ሁኔታ እንደምናየው ድሮ ከነበረበት ደረጃም በላይ በከፋ ሁኔታ ነው ያለው፤ ሕጋዊ ውሳኔ ተሰጥቶበታል::

በዚሁ መሰረት ውሳኔው ተከብሮ የተወረረው ሉዓላዊ መሬት ወደ ኤርትራ መካለል ነበረበት፤ አሁን ግን አልተቻለም።” ያሉት ኢሳያስ ፤ “ለምን አልተመለሰም ያልን እንደሆነ፤ የከሰረው ስብስብ [ህወሓት] የድንበርን ጉዳይ በአንድ በኩል እንደ ማስፈራሪያና በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መቋመሪያ ስለያዘ ነው:: በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በባድመ ጉዳይ ምን ሠራን ካልን፤ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ሳንገባ በአጭሩ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉ የችግሩን ምንጭ በዝርዝር አስረድተዋል።

“በአሁኑ ወቅትም ለጦርነቱ መነሻ በነበረችው ባድመ መሬት እየተሸነሸነ እየታደለ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ደግሞ የድንበሩን ጉዳይ እልባት ላለመስጠት ያለመ መሆኑን አመላክተዋል። ህወሓት በበኩሉ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የተወሰነውን የድንበር ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እንደሚቀበሉ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ውሳኔውን በተመለከተ ግልጽ ምላሽ አልሰጠም።

ሆኖም ጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔውን እንደሚቀበሉ ካሳወቁ ከአንድ ዓመት በኋላ የድንበሩን ጉዳይ ለመፍታት የተሰራ የሚታይ ነገር የለም። ለኤርትራ የተወሰነው የባድመ መሬት አሁንም በኢትዮጵያ እጅ ነው የሚገኘው።

ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክተው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “በባድመ ድንበር ብቻ ሳንታጠር፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በሁሉም አቅማችን እንደግፋለን ፤ ሰላም ሰርተህ የምታመጣው እንጂ እንደመና ከሰማይ የሚወርድ አይደለም”  ካሉ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመሩትን የሰላም ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ስምምነት ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን በመጠቆም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ፖለቲካዊ ለውጥም ኤርትራን እንደጎረቤት ሳይሆን ራሷን በቀጥታ ስለሚጎዳት “እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልም” የሚሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሦስት ትውልድ የተደረገው ጦርነት “ትርጉም አልባ ነበር” በማለት ጦርነቱም የውጭ ኃይሎች ጉዳዩን ስላወሳሰቡት የመጣ ጣጣ እንደነበርም ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY