ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቢሾፍቱ ባስ መገጣጠሚያ ሠራተኞች፣ የተገባልን የደሞዝ ጭማሪ ይፈፀምልን በሚል ምክንያት አራት አውቶቡሶችን ማቃጠላቸው እያነጋገረ ይገኛል።
ከ 10 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት ይህ ድርጅት በተደጋጋሚ የደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ለሠራተኞቹ ቃል ቢገባም መፈፀም አልቻለም። በዚህ ምክንያት ከሦስት ሳምንት በፊት በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ፋብሪካው የተነሳ በተቃውሞ ግርግር መካከል ፣ መኪኖቹ በእሳት መያያዛቸው ዘግይቶ ተሰምቷል።
ተገጣጥመው ሊሸጡ የተዘጋጁትን አራት አውቶቡሶች በሚቃጠሉበት ወቅት እሳቱን ለማጥፋት ሌሎች ሠራተኞች ቢረባረቡም፤ መኪኖቹ ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን የዐይን እማኞች ገልጸዋል። የሜቴክ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ መሐመድ እድሪስ ለአዲስ ማለዳ የድርጊቱን መፈጸም አረጋግጠው፣ እስከ አሁን ግን በጉዳዩ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም ብለዋል።
“ይሄንን ድርጊት በተቋሙ ላይ አሉታዊ አመለካከት እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት የፈጸሙት እንጂ የድርጅቱ ሠራተኞች ያደረጉት ነው ብለን አናምንም” ያሉት ሓላፊ “ነገር ግን ማንም ያድርገው ማን፣ ድርጊቱ ለድርጅታችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው” ካሉ በኋላ አውቶቡሶቹ ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመንም 3.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ተናግረዋል።
ሜቴክ 73 ቢሊዮን ብር እዳ እንዳለበት የገለፁት መሐመድ እድሪስ፣ በድርጅቱ ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ለችግሩ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ለባሰ ችግር እንደሚዳርገው እና የተፈፀመውም ድርጊት ወንጀል እንደሆነ ጠቅሰዋል።ድርጅቱ አቅም አንሶታል በሚልም ሠራተኞች ዝቅተኛ ደሞዝ እንዳላቸው በመታመኑ፣ ደሞዝ ለመጨመር መታሰቡ ለሠራተኞቹ ተነግሮ ነበር። እንደ ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ገለጻ፣ በእዳ ውስጥ ያለ ተቋም ሲያዝ የመጀመርያ ሥራ የሚሆነው ያለውን እዳ መቀነስ እንጂ ተጨማሪ እዳ ማምጣት መሆን የለበትም።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም ማስተዳደር ከሚችለው ውጪ በጣም ብዙ ተልዕኮዎችን ያቀፈ ሆኖ በመቆየቱ፣ ለሠራተኞቹ ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል። ድርጅቱ እንደ አዲስ ሲዋቀር ዋነኛ ሥራው ያደረገው የሠራተኛውን ድልድል በእውቀት ደረጃው በመመዘን የመዋቅር ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደነበረም ተሰምቷል ። አምራች ያልሆነ በብዙ ሺኅየሚቆጠር ሠራተኛን ይዞ መቆየት ያለፈው አመራር ድክመት ነበር ተብሏል።
በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውን የአውቶሞቲቭ መገጣጠሚያ ጨምሮ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎችን ያጠቃለለው ሜቴክ፣ የደሞዝ ጉዳይን በተመለከተ ሌላ ተቋም እንደሚፈፅም ተናግሯል። ይሄ ችግር ከኹለት ወር በላይ ይቀጥላል ብለው እንደማያስቡ አንስተው፤ በአጭር ጊዜ ወደ መፍትሄው ለመድረስ ኮሚቴ ተመሥርቶና እና አዲስ አደረጃጀት ተዋቅሮ መጠናቀቁን ገልፀዋል። አያይዘውም እንደ አዲስ የሠራተኞቹ ምደባ ተደርጎ፣ አዲስ የደሞዝ እርከን ወጥቶለት እየተስተካከለ መሆኑንም አመራሩ አስረድተዋል።