ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የምፅዋና የአሰብ ወደቦች የሚሰጡትን አገልግሎት የማሻሻል ሥራዎች እየሠሩ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ገለጹ። ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት ከኤርትራ ውስጣዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ትናንት ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።
የወደቦቹን አገልግሎት ውጤታማነት ለመጨመር የማደስ፣ የማስፋትና የማሳደግ ሥራዎች ለማከናወን እቅድ መያዙን ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።
“ወደቦቹን ስናሻሽል ኢትዮጵያን ብቻ እያሰብን አይደለም፤ ዋነኛ ትኩረታችን ቀይባሕር በቀጠናው ላይ ያላትን ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰፋ ያለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያለመ እቅድ ነው” ያሉት ኢሳያስ ከተጋገዝን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ስለምንችል በአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ውህደት መፍጠር አንዱ የመንግስታችን ዓላማ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከወደቦች በተጨማሪ ከመንገድ ግንባታ ጋር የተያዙ እቅዶችም ላይ መረጃ ሰጥተዋል:: በዚህም ኢትዮጵያንና ኤርትራን የሚያገናኙ መንገዶችም የሚያስፈልጋቸውን ጥገናም ሆነ ግንባታ ለመሥራት መንግሥታቸው ማቀዱን አመላክተዋል። በዚህ መሰረት ከአሰብ በደባየሲማ ኢትዮጵያን የሚያገናኘውን መንገድ የማስፋት፤ ከምጽዋ በደቀመኃሪ አድርጎ ዛላምበሳ፤ ከአስመራ በመንደፈራ፣ ራማን የሚያገናኙት የአስፋልት መንገዶች ደግሞ የማሻሻል ሥራዎች በዚህ አመት እንደሚጀመሩና፤ የተጀመሩትም እንደሚጠናቀቁ አረጋግጠዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን፣ ኢንቨስትመንት፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽ ሰጥተዋል። ለሁለት አስርት አመታት ሲንከባለል የመጣው የመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ማስተካከያ ጥያቄ ላይ ምላሽ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ ሠራተኞች አስፈላጊውን የኑሮ ወጪ የሚሸፍንላቸው በቂ ደመወዝ እንዳልነበራቸው አምነዋል። መንግሥታቸው ይህንን ችግር ለመፍታት ከሁለት አመታት በፊት የደመወዝ ማስተካከያ ማድረግ መጀመሩን እና፤ በደምወዝ ማስተካከያው ሂደት እስከ አሁን ጭማሪው ያልደረሳቸው የመንግሥት ሠራተኞች የሁለት ዓመት ድምር እንደሚደርሳቸውም ይፋ አድርገዋል።
መንግሥት የደመወዝ ማስተካከያ አሠራሩንም ለመተግበር እክሎች እንደገጠሙት የገለፁት ኢሳያስ አፈወርቂ ይህም በአገሪትዋ ተገቢ ባልሆኑ ምክንያቶች የሸቀጦች ዋጋ ንረት በመፈጠሩ መሆኑን ጠቁመው ፤ “መንግሥት ይህን ኢ-ምክንያታዊ የሆነ የዋጋ ንረትን በቸልታ አያልፈውም ፤ እርምት ይወስዳል” በማለት አስጠንቅቀዋል
ያለውን የዋጋ ንረት ለማስተካከልም ባለፉት ዓመታት መንግሥት የቤት ኪራይ፣ ስጋ እና የታሸገ ውሃ ላይ የዋጋ ተመን ማድረግ እንደጀመረ እየተነገረ ነው። የመኖርያ ቤቶች ግንባታ ዋነኛው የአገሪትዋ ቁልፍ ችግር እንደሆነ ያወሱት ፕሬዚዳንቱ ፤ መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ብሎ የጀመራቸው የቤቶች ግንባታ ቢጀምርም፤ ያላለቁ ቤቶች ግን በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በሂደትም መንግሥት ጥናት አካሂዶ አዋጪ ሆኖ ከተገኘ ፣ በቤቶች ግንባታ የውጪ ተቋራጮች ጭምር ለማሳተፍ ሀሳብ እንዳለ የገለጹት ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ፤ ያላለቁ እቅዶች ስላሉ በዚህ አመት የሚሠሩ ሥራዎችን ለማስቀመጥ ትንሽ ከባድ እንደሆነ በመጠቆም ዝርዝርም ሆነ ቀነ ገደብ ከማስቀመጥ ተቆጥበዋል።
ፕሬዚዳንቱ አንዳንድ አገሪቷ ያሉባትን ችግሮች በግልፅ ከመናገር ወደኋላ አላሉም:: በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት “አክስሮናል” ያሉትን የትምህርት ዘርፍ ፖሊሲ ለአገሪትዋ ኢኮኖሚ ዋነኛው ምሰሶ በመሆኑ ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ ይገባል ብለዋል:: በተጨማሪም ከቀይ ባህር በዓመት እስከ 100 ሺ ቶን የዓሳ ሀብት ማግኘት እየታቸለ ባለፉት 20 ዓመታት ግን አስር ሺ ቶን ብቻ እንደነበረ አስታውሰው ፤ይህንን የአሳ ሀብት ለማሳደግም አስፈላጊውን የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለማከናወን እቅድ መያዙን አብራርተዋል።