ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከየካቲት 5 እስከ 7 ለሚያደርጉት ጉብኝት እየተከናወነ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ውይይት መደረጉ ተሰማ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሀሙስ ጀምሮ ለሦስት ቀን የሚቆይ ጉብኝት ያደርጋሉ።
አርብ የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም በዱባይ ከተማ ሸባብ አልአህሊ ክለብ በአልመክቱም ስታዲያም በመገኘት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና በመካከለኛው ምስራቅ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መልእክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዝግጅቱን ለማስተባበር ከኅብረተሰብ አደረጃጀቶች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከልማት ማኀበራት የተውጣጣ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ ነው ተብሏል።
ከሰባቱም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲቀበሉና እንዲገናኙ ለማድረግ እየተከናወኑ ስላሉ እንቅስቃሴዎች ፣ መስተንግዶ እና የሎጀስቲክ ሥራዎች የሥራ ሂደት በተመለከተ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እና የዐቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ በተገኙበት ውይይት መካሄዱን ከዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ቆንስላ አስታውቋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ለመገናኘት ከየግዛቶቹ ወደ ዝግጅት ቦታው ለሚመጡ ዜጎች በየግዛቶቹ ከተሞች አማካይ ቦታዎች ላይ ነፃ የአውቶቡስ የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘጋጅቷል:: አውቶቡስ ማቆሚያ ቦታዎች እና አስተባባሪዎችን የተመለከተ መረጃዎች በቀጣይ ለኅብረተሰቡ ይገለጻል ነው የተባለው።