ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊታችን ሀሙስ በሚያደርገው አስቸኳይ ስብሰባው የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን የፊታችን ሀሙስ የካቲት 5 ቀን 2012 እንደሚያካሂድ ቅድመ መርሃ ግብሩ ያሳያል።
በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ፣ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ የወጣውን የአፍሪካ ህብረት የካምፓላ ስምምነትን መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ተገምቷል። በተጨማሪም የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የቀለም ጽሑፍ ኅትመት ሥፀራዎችን ተደራሽነትን ለማመቻቸት የወጣውን የማራካሽ ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያጸድቅም ነው የተሰማው።
የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአፍሪካ ህዝቦች እና ሰዎች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋዊያን መብቶች ፕሮቶኮል ስምምነት ለማጽደቅ፤ እንዲሁም የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅን በተመለከተ የቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ መርምሮ በተጨማሪነት እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።
የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውጭ አገራት ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነትን ጨምሮ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ምክር ቤቱ መቋጫ ያበጅለታል ተብሎ ተገምቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት እና የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራትም ሌሎች አጀንዳዎች ይሆናሉ ተብሎ ተገምቷል።