ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና የድርቅ ማካካሻ ላይ የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን፤ የህግና ቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ቢያደርጉም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ በጋራ ማዘጋጀት አልቻሉም::
ባለፈው ሳምንት አሜሪካና የአለም ባንክ በአደራዳሪነት በተገኙበት የሶስቱ ሃገራት የውጭና የውሀ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከህግና የቴክኒክ ባለሙያዎቻቸው ጋር በመሆን ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የአገራቱ ተወካዮች የግድቡን የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው በድርቅ ወቅት፣ ለዓመታት የተራዘመ ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅትና ለዓመታት የተራዘመ ደረቅ ወቅት ላይ ስለሚኖረው የውሃ አሞላልን በተመለከተ መሰረታዊ መግባባት ላይ ደርሰዋል መባሉም አይዘነጋም።
የውጭና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ወደ የአገራቸው ቢመለሱም የቴክኒክና የውሃ ባለሙያዎቹ በስብሰባው ለሳምንት ያህል ቀጥለዋል። ከሦስትዮሽ ምክክራቸው በኋላ በውሃ አሞላልና ድርቅ ማካካሻ ሰነድ ላይ ለመፈረም በነገው ዕለት ቀጠሮ በተያዘው መሰረት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ዋሽንግተን ዲሲ መግባታቸው ተሰምቷል::
ዶ/ር ስለሺ ዋሽንግተን ከገቡ በኋላም ከግብፅ እና ሱዳን ልዑካን ጋር የተደረገውን የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋር ገምግመዋል:: የልዑካን ቡድኑ በውሃ አሞላልና ድርቅ ማካካሻ ጉዳዮች ላይ ውይይት ቢያደርግም፣ ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ በጋራ ማዘጋጀት አለመቻሉን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ይፋ አድርገዋል።
በሦስቱ አገራት መካከል በህዳሴው ግድብ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር በጥር ወር አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፤ በተደራዳሪዎቹ መካከል ከስምምነት ላይ ባለመደረሱ እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ ለመዝለቅ ተገዷል። አገራቱ በተለይ ከስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ያደረጋቸው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማውጣት እየገነባቸው ያለው ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ነው።
ግብጽ የውሃ ሙሌቱ እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ እንዲሆን ስትጠይቅ፤ ኢትዮጵያ ግን ሙሌቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ትፈልጋለች። በድርድሩ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው የኢትዮጵያና ግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም የየአገራቱ የህግና የቴክኒክ አማካሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ከኢትዮጵያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን፤ ግብጽ ደግሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹክሪና የመስኖ ሚኒስትሩ ሞሐመድ አብደል አቲ በዋሽንግተኑ ውይይት ላይ በመሪነት ሲሳተፉ ቆይተዋል። አሜሪካና የዓለም ባንክ በተዳራዳሪዎች ላይ ጫና አሳድረዋል፤ እንዲሁም ለግብፅ ወግነዋል የሚሉ መረጃዎችም ሲወጡ የነበረ ቢሆንም አቶ ፍፁም ኢትዮጵያ በጥቅሟ እንደማትደራደር አሳውቀዋል።
“ኢትዮጵያ በፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የምታምን ሲሆን፤ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም” በሚል አስፍረዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ድርድሩ “በግድቡ ብቻ ላይ የተወሰነ መሆኑን፣ እንዲሁም የአገራችንን ነባርና የወደፊት በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብትን በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይቀየር አቋም ነው” በማለት መግለጹ አይዘነጋም::