ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመሬት ወረራ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፈተና እየሆነ መጥቷል ተባለ። የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር በተመለከተ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፋ ያለ ምክክር አድርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሚመለከታቸው አካላት እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በውይይት መድረኩ ተሳታፊ ሆነዋል። በውይይቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለው የመሬት ወረራ ለከተማው አስተዳደር ፈተና እየሆነ መምጣቱ ተጠቁሟል። ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ የመረጃ አያያዝ ማነስ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ችግሮች ከህግ ሥርዓቶች አለመከበር ጋር ተዳምረው ለመሬት ወረራው መስፋፋት ምክንያት ሆነዋል ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ቢሮ፤ በከተማዋ ህገወጥ የመሬት ወረራ እና ተያያዥ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓቱን የማዘመን ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ይህን ይበል እንጂ የከንቲባ ታከለ ኡማን ሹመት ተከትሎ ከተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች በተደራጀና በስውር ግንኙነት ድጋፍ የሚደረግለት የሰው ኃይል በሐያት ጎሮ፣ በጀሞ ፣ መካኒሳ ፣ አሸዋ ሜዳ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ አካሂዷል።
ራሱን ቄሮ በማለት የሚጠራው እና የለውጡ ብቸኛ ወላጅ አድርጎ የሚያስበው ቡድን ግልጽ የሆነ ህገ ወጥ የሆነ የመሬት ወረራ ሲያካሂድ አንዳችም እርምጃ ለመውሰድ ልቡ ያልጨከነው እና ችግሩ አሁን ድረስ እንዲዘልቅ ዓይነተኛ ሚና በተዘዋዋሪ ተጫውቷል የሚባለው የታከለ ኡማ የአዲስ አበባ መስተዳደር ዛሬ ላይ ጉዳዮ አሳስቦኛል ማለቱ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል።