ሱዳን አል-ቃይዳ ለገደላቸው አሜሪካውያን ቤተሰቦች ካሳ ልትከፍል ነው

ሱዳን አል-ቃይዳ ለገደላቸው አሜሪካውያን ቤተሰቦች ካሳ ልትከፍል ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሱዳን እአአ 2000 በየመን ወደብ አል-ቃይዳ በተፈጸመው ጥቃት ለተገደሉ 17 አሜሪካውያን ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማማች። ሱዳን በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት የምትሻ ከሆነ ይህን ካሳ መክፈል እንደሚጠበቅባት በአሜሪካ እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦላት እንደነበር ይታወሳል።

ጥቃቱን የሰነዘሩት ሁለቱ አጥፍቶ ጠፊዎች ሥልጠና የወሰዱት በሱዳን ስለሆነ ለጥቃቱ ሓላፊነቱን የምትወስደው ሱዳን ነች ስትል አሜሪካ ደምድማለች። ሱዳን ይህ ጥቃት እንዲፈጸም ለአል-ቃይዳ እና ቢን ላደን የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጋለች ተብሎ ይታመናል።

በተጨማሪም አሜሪካ አጥፍቶ ጠፊዎቹ በሱዳን ልምምዶችን ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ በሱዳን የንግድ ሥራ እንዲያከናውኑ እና ተቀጣጣይ ነገር ይዘው በሱዳን ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዶላቸው ነበር።

አዲሱ የሱዳን መንግሥት በአሜሪካ ተጥሎበት ያለውን ማዕቀብ ማስነሳት ለነገ የማይለው ዋና እቅዱ አድርጓ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሱዳን ለሟች አሜሪካውያን ቤተሰቦች ምን ያህል ገንዘብ ለመክፈል እንደተስማማች ይፋ ባይሆንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ የዘገበው ሮይተርስ፣ ምናልባት ከ30 ሚሊዮን ዶላር እንደማያንስ ይገመታል ብሏል።

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ካውንስል የቀድሞ መሪውን አል-በሽርን ለዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፎ እንዲሰጡ መወሰኑ ይታወሳል። የሽግግር ካውንስሉ ይህን ውሳኔ የወሰደው የአሜሪካን ፍላጎትን ለሟሟለት ነው የሚሉት በርካቶች ናቸው።

ከአንድ ሳምንት በፊት ታሪካዊ በተባለ ሁኔታ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ካውንስል ሰብሳቢ አብድል ፈታህ አል-ቡረሃን በኡጋንዳ ኢንቲቤ ተገናኝተው መምከራቸው ይታወሳል። ከሁለቱ መሪዎች ውይይት በኋላ ሱዳን እና እስራኤል ግንኙነት ለመጀመር መስማማታቸው እየተነገረ ነው።

የሱዳን የኢንፎርሜሽን ሚንስትር ለአሶሲዬትድ ፕሬስ እንደተናገሩት ከሆነ ከሱዳን ሌላ በኬንያ እና በታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ አል-ቃይዳ ባደረሳቸው ጥቃቶች ለሟች አሜሪካውያን ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ውይይት እየተደረገ ነው ።

በኤምባሲዎቹ ላይ በደረሰው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በወቅቱ የአል-ቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን እአአ በ1990ዎቹ የፕሬዝደንት አል-በሽር እንግዳ ሆኖ በሱዳን ለአምስት ዓመታት ኖሯል። በዚህ ሱዳን 1993 ላይ የአሜሪካ አሸባሪ አገራት ዝርዝር ውስጥ ተካተተች። የሱዳን መንግሥት ግን በእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ እጁ እንደሌለበት በተደጋጋሚ እየተናገረ ይገኛል።

“ይህን ካሳ ለመክፈል የተስማማነው ሱዳንን ከዝርዝሩ ውስጥ ለማስወጣት በአሜረካ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት እና ከአሜሪካ እና ከተቀረው ዓለም ጋር መልካም ግነኙነት ለመፍጠር ነው” ሲል የሱዳን መንግሥት መግለጫ አውጥቷል። በ2000 ላይ የመናዊ የሆኑ አጥፍቶ ጠፊዎች እስከ 225ኪ.ግራም የሚመዝን ተቀጣጣይ ፈንጂ በመጠቀም በአሜሪካ መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። በዚህ 17 መርከበኞች ሲሞቱ ከ40 በላይ በሚሆኑት ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል። አሜሪካ ከዚህ ጥቃት ጋር ግንኙነት ነበረው ያለችውን ጀማል አል-ባዳዊ የተባለን ግለሰብ ከ19 ዓመታት በኋላ ባሳለፍነው ዓመት የመን ውስጥ በአየር ጥቃት ገድላዋለች።

LEAVE A REPLY