በህዳሴው ግድብ ላይ ሱዳን ለግብፅ ድጋፏን መሰጠቷ ተነገረ

በህዳሴው ግድብ ላይ ሱዳን ለግብፅ ድጋፏን መሰጠቷ ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሱዳን በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የቆየው የህዳሴ ግድብ ድርድር ዋነኛ ትኩረቱን በመሳት ወደ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ ሄዷል ተባለ::

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ የዘገበው ቢቢሲ፤ ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗን፣ እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብጽ መወገናቸውን ጠቁሞ አሁን ላይ ጉዳዩ “4 ለ 1” ሆኗል በማለት ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።

አሜሪካ እና ዓለም ባንክ በግድቡ ዙሪያ እጃቸውን እንዲያስገቡ መፈቀዱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ውስጥ አዋቂ ለቢቢሲ ተናግረዋል::

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ከሁለት ቀናት በፊት ተደራዳሪ ቡድኑ ”በብዙ ጉዳዮች ላይ የመከረ ቢሆንም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ ማዘጋጀት አለመቻሉ ታይቷል” ብለው መናገራቸውም መረጃውን ወደ እውነታ ያስጠጋዋል።

ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት የሰነዱ አብዛኛው ክፍል የቀረበው በአሜሪካ በመሆኑ፤ ትኩረቱም ስለ ግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በመሆን ፈንታ፤ ማን ምን ያህል የውሃ ድርሻ ይኑረው? የሚለው ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ከስምምነት መድረስ እንዳልተቻለ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት ባለሙያ ገልፀዋል። በግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያ የህግ አርቃቂ ቡድን አሁንም አሜሪካ እንደሚገኝ በማስታወስ፤ በውሃ ክፍፍል ላይ ለመነጋገር እንደ አገር ዝግጁ አይደለንም፤ የድርድሩ አላማም ይህ አይደለም ብለዋል።

ከግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ በድርቅ፣ በረዥም ጊዜ ድርቅ እና በተከታታይ ድርቅ በሚሉት በሰነዱ ላይ በሰፈሩት ቃላቶች ትርጓሜ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም። ስለዚህም የኢትዮጵያ የህግ አርቃቂዎች በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሰነዱ ላይ የሰፈሩ በርካታ ነጥቦችን በጥያቄ ምልክት ውስጥ ለማስቀመጥ ተገድደዋል መባሉም ተሰምቷል።

“ትልቁ ነገር ሰነዱ የውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ ሊያተኩር አይገባም ነበር። ወደ አሜሪካ የሄደው የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ቡድንም የውሃ ድርሻ ክፍፍል ለመነጋገር ስልጣን አልተሰጠውም። ስለ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ብቻ ሳይሆን ከአስሩም የተፋሰሱ አገራት ጋር ነው መነጋገር ያለባት” የሚሉት ባለሥልጣን፤ ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍን ፈርማ ያፀደቀች አገር መሆኗን እና ይህ ስምምነት ሳይጣስ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ባሉበት መነጋገር እንደሚገባት አታውሰዋል።

 

LEAVE A REPLY