ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በተከሰተ ሁከት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የራቁ 746 ሺህ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ የሚያስችል መርሃ ግብር ይፋ ተደረገ።
መርሃ ግብሩ ኢዱኬሽን ካን ኖት ወይት በሚባል ድርጅት የቀረበ ሲሆን፤ በ728 ትምህርት ቤቶች በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ተማሪዎችን ያካትታል መባሉም ተሰምቷል። በትምህርት ሚኒስቴር የበላይነት የሚመራው ይህ አዲስ መርሀ ግብር በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በ44 ወረዳዎች የሚተገበር ነው።
ለእውቀት ማዕድ መርሃ ግብሩ 165 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል:: ከዚህ ውስጥ 27 ሚሊየን ዶላሩ አሁን ላይ መለቀቁ ተገልጿል። ቀሪው 138 ሚሊየን ዶላር በሦት ዓመታት ውስጥ የሚለቀቅ ሲሆን፤ ተጠቃሚ ከሚሆኑት 746 ሺህ ህጻናት ውስጥ 365 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ ታውቋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ጺዮን ተክሉ፥ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ሁከቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ህጻናት የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል:: የመርሃ ግብሩ ባለቤት የኢዱኬሽን ካን ኖት ወይት ዳይሬክተር ያስሚን ሸሪፍ በበኩላቸው ፤ መርሃ ግብሩ በጥቃት፣ በድርቅ፣ በመፈናቀልና በሌሎች ሁከቶች የተጎዱ ህጻናትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።