ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተበራከቱ በመጡ የወንጀል ተግባራት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር በማዋል ክስ መመስረት መጀመሩን ገለጸ።
የሕግ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ በብሔር ወይም በክልሎች መካካል፣ እንዲሁም በግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጠር ግጭት መነሻነት ወንጀል በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በማድረግ፣ የተደራጀ የምርመራና ክስ የመመስረት ሂደት መጀመሩን አስታውቋል።
በግጭቶቹ ላይ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ከሚገኙባቸው ስፍራዎች መካከልም ምዕራብ ጉጂ፣ አዳማ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ አርሲ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ እና አዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ በመግለጫው የተጠቀሱ ሲሆን፤ ከደቡብ ክልል ደግሞ ጌዲኦ ዞን፣ ሀዋሳ፣ የቴፒና ሸካ ዞን ተካተዋል።
ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ የተጀመረባቸው ሌሎች አካባቢዎችም በመግለጫው የሰፈሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በጅግጅጋና ሌሎች ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ካማሽ ዞን፣ መተከል ዞን በግንባር ቀደምትነት ተቀምጠዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን በጃዊ ወረዳ፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ በሃይማኖት ተቋማት ፤ እንዲሁም በአንዳንድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተፈጸመውን ወንጀል ድርጊቶችን መነሻ በማድረግ ተጠሪጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ መጀመሩን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጠቁሟል።
ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው ላይ የመንግሥት ከፍተኛ አመራር ባደረገዉ ግምገማ በየቦታው የሚፈጠሩ የወንጀል ድርጊቶች ዋነኛ ችግር የፖለቲካ አመራሮች እጅ ያለበት መሆኑን በሚገባ መረዳቱንም አጋልጧል። ይህን እኩይ ተግባር ሲያስፈጽም እና ሲፈፅም በዝምታ ሲያልፍ የነበረው አመራር ከድርጊቱ እንዲታረምም መግለጫው አሳስቧል።
“በአገሪቱ በሚፈለገው መጠን የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የነበረውን ፈተና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የምንሻገረው እንደሚሆን እሙን ነው” ያለው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎች በሕግ ፊት እንዲቀርቡ የሚደረገውን ጥረት በሚያደናቅፉ አካላት ላይ ያለምንም ምህረት በማያዳግም ሁኔታ ተጠያቂ እንደሚደረግ አስረድቷል።
“የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ለድርድር አይቀርብም” ያለው የሕግ የበላዮ ተቋም ፤ ለአገሪቱ ደህንነትና ለሕዝቦች ህልውና ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን እንደማይታገስ ጽኑ አቋም መያዙን በመግለጫው ላይ አጽንኦት ሰጥቶበታል።