ምርጫ ቦርድ የክረምቱን ዝናብ ምክንያት በማድረግ የምርጫውን ቀን አራዝሚያለሁ አለ

ምርጫ ቦርድ የክረምቱን ዝናብ ምክንያት በማድረግ የምርጫውን ቀን አራዝሚያለሁ አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ነሐሴ 10 የድምጽ መስጫ ቀን ይሆናል ተብሎ ሃሳብ ቀርቦ የነበረ  ቢሆንም፤ የድምጽ መስጫ ቀኑ በአስራ ሦስት ቀናት ተገፍቶ በነሐሴ ወር መጨረሻ እንደሚካሄድ ታወቀ።

በብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው የ2012 አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነሐሴ 23/2012 ዓ.ም ድምጽ መስጫ ቀን ሆኗል። ቀደም ሲል ለውይይት በቀረበው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ የተለያዩ ወገኖች ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ለመራጩ አስቸጋሪ ይሆናል በሚል ቅሬታ የቀረበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፣ አሁን በወጣው መረሃ ግብር  መሰረት ምርጫው የሚካሄድበት ቀን በ13 ቀናት ወደፊት ተገፍቷል።

የምረጫው ዕለት ወደ ፊት ለመገፋቱ እንደምክንያት የቀረበው በነሐሴ አጋማሽ ላይ ከሚኖረው ዝናብ ይልቅ በወሩ መጨረሻ ላይ የዝናቡ ሁኔታ ይቀንሳል በሚል እንደሆነም ተጠቁሟል።

ለሁለተኛ ጊዜ በተለወጠው መረሃ ግብሩ መሰረት መጋቢት 01 የምርጫ ክልል ካርታ ይፋ የሚደረግ ሲሆን ፤ ይህንንም ተከትሎ የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር መጋቢት 28 ቀን ለሕዝብ ግልጽ እንደሚደረግ ታውቋል። በአገራዊ ምርጫው ድምጽ የሚሰጡ መራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 14 እስከ ግንቦት 23 ድረስ የሚካሄድ ሲሆን ፤ በምርጫው የሚወዳደሩ እጩዎች ምዝገባ ደግሞ ከግንቦት 05 እስከ 19 እንደሚሆን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በተያያዘ የምርጫ ቅስቀሳ የሚካሄደው ከግንቦት 21 እስከ ነሐሴ 18/2012 ድረስ ባለው ለሦስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ እንደሚሆን ይፋ የተደረገው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አመልክቷል።

በዚህ መሰረት ከነሐሴ 19 እስከ የድምጽ መስጫው ቀን ዋዜማ ድረስ የምርጫ ቅስቀሳ የማይደረግባቸው ቀኖች  እንደሆኑና ነሐሴ 23 ቀን መራጮች ድምጻቸውን የሚሰጡበት የምርጫ ቀን ይሆናል ተብሏል። ከነሐሴ 24 እስከ ጳጉሜ 03/2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተረጋገጡ የምርጫ ውጤቶች ይፋ የሚደረግባቸው ቀናት እንደሚሆኑ ቦርዱ ከወዲሁ ይፋ አድርጓል።

ዛሬ የተገለጸው የፕሮግራም ማሻሻያ የ2012 የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የመጨረሻው ይሁን ወይም ከፓርቲዎች ጋር በሚደረግ ውይይት ማስተካከያ ማድረግ የሚቻልበት አይሁን በወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው ምርጫ ቦርድ ግልጽ ያለ ማረጋገጫ አልሰጠም::

LEAVE A REPLY