ያኔ ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ ብቅ ብቅ ሲሉ “በአሮን እና ሙሴ “ሲመሰሉ ለማመስገን የተቸገርኩ እኔ ነበርኩ። ቀስ ማለት ደግ እንደሆነ ረጃጅም ፅሁፎች ስሞግቶ የነበርኩም እኔነኝ። ከጅምሩ ከፊል ተስፋ እንጅ ከሰው ፍፅምናን መጠበቁ ጥሩ እንደማይሆን ይሰማኝ ነበር። አሁንም ከአብይ አስተዳደር እንከን እንደማይጠፋ በማመን እኖራለሁ። ተስፋየ ሲጎድል ሲሞላ እውላለሁ፣በዚህ ሁሉ ውስጥ ኢትዮጵያን አያለሁ።
ጠ/ሚ አብይን የኢትዮጵያን ክፉ በመሻት አላማቸውም። ለህልውናዋ ከዚህ በበለጠ ቢሰሩ እመኛለሁ፣ ከበሮ በሰው እጅ እንደሚያምር ሲይዙት እንደሚያደናግር ስለማውቅ አብይ በበቂ ሁኔታ ባልሰሩት ነገር ስወቅስ የተረከቡት ሃገር የተተበተበበትን ችግርም እረዳለሁ። ስለዚህ ሲያጎድሉ ብወቅስም የሚያደርጉትን በጎ ነገርም አደንቃለሁ፣ የገቡበት መቃተት ይገባኛል!
በዚህ ንግግራቸው በሃገራቸው ልጆች ክብር መጉደል እንደ ሃገር ልጅ እንደሚያስቡ፣ለሃገራቸው ቅንዓት ያላቸው ሰው እንሆኑ እንደ ንጉስ ርቀው ሳይሆን በሰው ሰውኛ ሲናገሩ ቀድሞ እንዲህ ያለ ክብር አይተው ለማያውቁ የሃገራችን ልጆች መልካም ነገር ነው።
አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በሃላ አረብ ምድር ይኖሩ የነበሩ(በሃገራቸው ኢንበሲ ፊት ለፊት ሳይቀር እንደ ውሻ ሲጎተቱ የነበሩ ወገኖቻችን) የተሻለ ክብር እና የስራ ሁኔታ እንዲያገኙ መደረጉ ጠ/ሚው ሊመሰገኑበት የሚገባ ነገር ነው።ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ የዕምነት ቦታ ማስፈቀድ መቻላቸውም እንዲሁ። ሃገር ቤት ባለው የቤተክርስቲያኗ ስጋት እኔም ተቃውሞ አለኝ ነገር ግን በጎ ነገር ሲደረግም እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።
ሰውን መተቸት ብቻ ጠንካራ አያደርገውም።ትችት ብቻ እንደውም የአቅምሙን ያህል መስራትም የማያችል ደንጋራ ነው የሚያደርገው። አብይ ሲያጠፉ የምናብጠለጥለውን ያህል ለሃገራቸው ልጆች ጊዜ ሰጥተው፣ አክብረው፣ እንዲህ መንፈስ የሚያድስ ንግግር ስላደረጉ መበረታታት አለባቸው። ከብዙ መልካም ነገር ጥቂት ሃረጎችን አውጥቶ ትችት ብቻ ማዝነብ የበጎነት ምልክት አይደለም።
በዚህ ንግግራቸው በሃገራችን ያለው የመባላት ፖለቲካ ምን ያህልና እንዳማረራቸው፣ እንደ ታከታቸው ጭምር ያስረዳል! ሆኖም አሳልፈው ተስፋ ያያሉ፣ ሃገር ሃገር ሲሉ አብሮ አለማለት አይቻልም!