ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የተመለከተ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ግድቡን በተመለከተ እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች አካሄድ እና አቅጣጫ ላይ ምክክር እንደተደረገበት ታማኝ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
በውይይቱ ሚኒስትሮች፣ የተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ገልጿል።
እኤአየካቲት 12 እስከ የካቲት 13 ቀን 2020 በዋሽንግተን ዲሲ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅን በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ሳይቋጭ መቅረቱ አይዘነጋም።
በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ እና ሱዳን ልዑካን ጋር የተደረገውን የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት በዋሽንግተን ዲሲ ከገመገመ በኋላ ሌላ ዙር ውይይት ሲካሄድ ነበር።
ይሁን እንጂ አገራቱ የግድቡን የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ሳይቋጭ መቅረቱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ገልጸዋል።
ዛሬ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በተካሄደው ውይይት ላይ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ አደራዳሪ በሆኑት አሜሪካና የዓለም ባንክ ቀጥተኛ ተፅእኖ ሱዳን ለግብጽ መወገኗን ተከትሎ ወደ አሳሳቢ ደረጃ የደረሰውን ጉዳይ አስመልክቶ ኢትዮጵያ በቀጣይ ምን አይነት አቋምና አማራጭ ይዛ እንደምትቀርብ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በዝግ እየመከሩ መሆናቸውን የውይይቱ ታዳሚ ምንጮቻችን ለኢትዮጵያ ነገ ተናግረዋል::