ሰራዊት ፍቅሬ፣ አየለ ጫሚሶና ሳምሶን ማሞ ለዲፕሎማሲ ቡድን በአገራዊ ስልጠና ላይ...

ሰራዊት ፍቅሬ፣ አየለ ጫሚሶና ሳምሶን ማሞ ለዲፕሎማሲ ቡድን በአገራዊ ስልጠና ላይ ተሳትፈዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት በአገሪቱ ዲፕሎማሲ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው ተባለ።

በስልጠናው ላይ ከህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት በመፍጠር በሕዝብ ገንዘብና ሞራል ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ድርጊት በመፈፀም የሚከሰሱት ሰራዊት ፍቅሬ እና ሳምሶን ማሞን ጨምሮ በፖለቲካ ቁማርተኝነተቸው የሚታወቁት አቶ አየለ ጫሚሶ መሳተፋቸው አግራሞትን ፈጥሯል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት የሚሰጠውን የአንድ ቀን ስልጠና ዛሬ ጠዋት ባስጀመሩበት ወቅት፤ ቡድኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የአገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባት በኩል በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን በማስታወስ በዚሁ ሥራ ለሚሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራን ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ ለማከናወን መሰል ስልጠናዎች ወሳኝ መሆናቸውን አቶ ገዱ ተናግረዋል።

ሥራውን በአግባቡ እና በተደራጀ መልኩ ለማከናወን እንዲቻል በመስኩ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የዘርፉን ጽንሰ ሐሳብ እና በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሙያው በቂ እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ባላቸው ምሁራን ስልጠናው እንዲሰጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።

ስልጠናው በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕለማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል እና በውጭ ግንኙነት ማሰልጠኛ ኢኒስቲቲዩት በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ስልጠናው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የድንበር ተሻጋሪ ሀብቶችና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ በምትከተለው አቅጣጫ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምንነት እና ጠቀሜታው፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል እና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በአገሪቱ የሚገኙ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የምርምር ተቀማት ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ ባለሀብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን በማካተት የተቋቋመ ነው ተብሏል። ቡድኑ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ በግብጽ፣ በሱዳን፣ በጅቡቲ፣ በኡጋንዳ እንዲሁም በቅርቡ በኤርትራ በመንቀሳቀስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማጠናከር እና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የመገንባት ሥራ በማካሄድ ላይ ነው።

በቡድኑ ምንም አይነት የሞራል ልእልና የሌላቸው ግለሰቦችን መካተት በዲፕሎማሲ እድገት ረገድ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ጠባሳ እንደሚጥል የጠቆሙ አስተያየት ሰጪዎች እንደነሰራዊት ፍቅሬና ሳምሶን ማሞን አይነት በሕዝብ ላይ ሲሳለቁ የነበሩ ግለሰቦች ከእንዲህ አይነት ከፍተኛ ሓላፊነት ማራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተቀዳሚ ስራ መሆን ይገባዋል ብለዋል።

LEAVE A REPLY