ዛዲግ አብርሃና አረጋዊ በርሄ ለደብረፂዮን ዛቻ ምላሽ ሰጡ

ዛዲግ አብርሃና አረጋዊ በርሄ ለደብረፂዮን ዛቻ ምላሽ ሰጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 45ኛ አመት የካቲት 11 ቀን 2012 ባከበረበት ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል፤ “በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አስጊ ነው፣ አገሪቱም ወደ መበታተኑ እያመራች ነው፤ ሠላም ጠፍቷል፣ ለውጡም አቅጣጫውን ስቷል” በማለት ያደረጉት ንግግር ከትግራይ ተወላጆች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡

ደብረፂዮን በፓርላማ ለሚገኙ የትግራይ ተወካዮች ባስተላለፉት መልዕክታቸው፤ ‹‹የሥልጣን ጊዜያችሁ ከማለቁ በፊት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ጣልቃ ገብነት፣ በተለይም ትግራይን በተመለከተ በመሪዎች ደረጃ የተሰጡት የጥላቻና የፀረ – ሕዝብ ንግግሮችን በይፋ ኮንኑ፤ ይህ የማይሆን ከሆነም፣ ትግራይ ራሷን የቻለች አገር መሆኗን አውጁ፤ ሀገር በመበተን ሂደት ተሳታፊ ነበሩ ተብላችሁ በታሪክ እንዳትወቀሱ ግዳጃችሁን ተወጡ ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል በትግራይ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት የካቲት 11ን አስመልክቶ ለትግራይ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ህዝቡ ለአገራዊ አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሌሎች አካላት በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘሩ የጥላቻ መልዕክቶች እንዲቆሙም የትግራይ የብልጽግና አመራሮች መጠየቃቸውም አይዘነጋም፡፡

የሕዝብን ተጋድሎ ከንቱ የሚያደርግን ያልተገባ የፖለቲካ ጨዋታን የትግራይ ወጣቶች እንዲረዱና እንዲሁም ለሁሉም በእኩል የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት ከሚደረገው ጥረት ጎን እንዲሰለፉም ጽ/ቤቱ ጠይቋል፡:

የህወሓት መስራች አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ “ደብረፂዮን ከፈለገ ብቻውን ይገንጠል፤ የትግራይ ህዝብ አሁን ያለው ችግር ውስጥ ነው፤ አብዛኛው እየኖረ ያለው በምግብ ለስራ ነው፤ በእርዳታ እየኖረ ያለውን ህዝብ ልክ እነሱ እያኖሩት ያለ ይመስል ወደ እሣት ለማስገባት መነሳታቸው እጅግ አሳዛኝ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የህወሓት አባልና የህወሓትን አካሄድ ተቃውመው ከፓርቲው የለቀቁት በአሁኑ ወቅት በዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል በሚኒስትር ማዕረግ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ “ትግራይ ውስጥ የጦርነት ጉሠማ እየሠማን ነው፤ ይህ የጦርነት ጉሠማ ዞሮ ዞሮ የሚበላው መሄጃ የሌለውን ድሃውን የትግራይ ህዝብ እንጂ በአውሮፓ ተቀማጥለው የሚኖሩትን የስብሃት ነጋ ልጆች አይደለም፤ ይሄን የትግራይ ህዝብ ልብ ሊል ይገባል” በማለት የቀድሞ ድርጅታቸውን ሴራ አጋልጠዋል::

LEAVE A REPLY