ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚነገርለት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በደብረ ብርሃን ከተማ አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን ቅዳሜ እና እሁድ ካካሄደ በኋላ አዳዲስ አመራሮችን መርጧል።
በዚህም መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው ፓርቲውን ከምስረታው ጀምሮ በሊቀ መንበርነት ሲመሩት የቆዩትን ደሳለኝ ጫኔን (ዶ/ር) አንስቶ በምትካቸው ምክትላቸው የነበሩትን አቶ በለጠ ሞላን ሊቀ መንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን፤ አቶ ዩሱፍ ኢብራሂምን ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር አድርጎ ሾሟል።
አዲሱ ሊቀ መንበር አቶ በለጠሞላ፣ በወርሃ ነሐሴ ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበው አጠቃላይ ምርጫ ጋር በተገናኘ ፓርቲው የበለጠ ዝግጅት ለማድረግ ያግዘዋል ተብሎ ስለታሰበ የተካሄደ የአመራር ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል።
“የተለየ ምክንያት የለውም፤ አስቸኳይ ጉባዔ ተጠርቶ ስብሰባ አድርገን ምርጫ እየመጣ ስለሆነ እስከዛሬ ከነበረን ዝግጁነት በላቀ ተዘጋጅተን ለመጠበቅ ፍላጎት ስለነበረን ከዚሁ አንፃር የተቃኘ ነው” በማለት አቶ በለጠ የአመራር ለውጥ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክያት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ በለጠ የቀድሞውን ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔን (ዶ/ር) “ጠንካራ መሪያችን ነበር” ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን፤ የቀድሞ ሊቀ መንበር ወደፊት በፓርቲው ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚና አስመልክቶ “አሁንም ከኋላ ሆኖ ሐሳብ በመስጠት፣ በአማካሪነት እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ ይቀጥላል” ነው ያሉት:: “ሰላማዊ ሽግግር ነው ያደረግነው። በእርሱ ጥቆማም ነው ይህ ሽግሽግ የተካሄደው“ በማለት የዶክተር ደሳለኝን ሚና ለማጉላት ሞክረዋል።
በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙሃን ላይ በፓርቲው አመራሮች ዘንድ ክፍፍል ስለመኖሩ አስተያየቶች መኖራቸውን የገለፁት አዲሱ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር፤ አስተያየቶቹን ፍሬ የላቸውም በማለት አጣጥለዋቸዋል።
“ጥሩ መንፈስ ላይ ያለ ፓርቲ ነው። ለመጪውም ምርጫ ሰፊ ዝግጅት እያካሄደ ነው። ከዚህ ውጭ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚናፈሱ ወሬዎች ምንጫቸው ከየት አንደሆነ አናውቅም” ያሉት አቶ በለጠ ሞላ፤ ፓርቲው ጠንካራ ሆኖ እንዳይወጣ የሚፈልጉ አካላት የሚያደርጉት ዘመቻ አካል ነው ሲሉም ተከራክረዋል።
ከሓላፊነታቸው የተነሱት የቀድሞ የአብን ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ አዲስ በተዋቀረው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ያልተካተቱ ሲሆን ፓርቲው ውስጥ በቀጣይ ስለሚኖራቸውም ድርሻ በጉባዔው ምንም የተገለጸ ነገር የለም:: ዶክተሩ አብንን በሚመሩበት ወቅት ፓርቲውን በአማራ ሕዝብ ዘንድ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጠንካራ ሥራ ቢሰሩም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማስቆም በማውገዝና የታሰሩ አባላትን በማስፈታት ረገድ መለሳለስ ይስተዋልባቸዋል በሚል በፓርቲው አመራሮች ዘንድ ተደጋጋሚ ትችትና ወቀሳ ይቀርብባቸው እንደነበር ለአብን ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል:
የንቅናቄው ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ 9 አባላት ያሉትን የፓርቲውን ሥራ አስፈጻሚ አመራሮችንም መርጧል። ከእነዚህም መካከል ከሰኔ 15ቱ የከፍተኛ የመንግሥት እና የመከላከያ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተገናኘ በእስር ላይ የሚገኙትን አቶ ክርስቲያን ታደለን የሥራ አስፈጻሚ አባል እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አድርጎ መርጧል።
“አመራሮቻችን እና አባሎቻችን በዚህ ጉዳይ ውስጥ እንደሌሉበት ማንም ሰው ያውቃል፤ የፖለቲካ እስር ነው የተፈፀመባቸው” ሲሉ ለነክርስቲያን ታደለ ፍትህ እጦት የተሟገቱት አዲሱ የአብን መሪ
በታሳሪዎቹ ዙሪያ ከመንግሥት አካላት ጋር የተለያዩ ያልሰመሩ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ግን ከምርጫው መቃረብ ጋር በተያያዘ መንግሥት ለምርጫ የሚያስፈልገውን ፖለቲካዊ መነቃቃት ተገንዝቦ ይለቃቸዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው እንዲሁም አቶ ክርስቲያን ታደለ ” የፓርቲው አመራር ሆነው ይቀጥላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።