ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ30 የኢትዮጵያ ወረዳዎች የኩፍኝ ወረርሽኝ መከሰቱን አስታወቀ። እስካሁን ድረስ አምስት ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት መሞታቸው ተነግሯል።
ሦስቱ የሞቱት ሰዎች ወረርሽኙ በተከሰተባቸው 30 ወረዳዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ መሆናቸውን የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት እና ምላሽ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ 30ዎቹ ወረዳዎች በስድስት ክልሎች የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህም ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ትግራይ መሆናቸው ታውቋል። ኃላፊው ለቢቢሲ እንደገለፁት፤ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ወረዳዎች የሚገኙት በገጠራማ የክልሎቹ አካባቢ ነው:: በወረርሽኙ የተጎዱት አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የሚገኙት ደግሞ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
አቶ መስፍን ጨምረው እንዳሉት፤ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው አካባቢዎች የክትባት ስርጭቱ ደካማ የሆነባቸው ናቸው።በዚህ ሳምንት ብቻ 228 በኩፍኝ የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸው ታውቋል።የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኩፍኝ ወረርሽኝ የተከሰተው ባለፈው ሕዳር ወር ላይ ነው። ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በኩፍኝ ምክንያት የሰዎች ሕይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።
በወቅቱ በርካቶች በወረርሽኙ መያዛቸውንና በአንዳንድ ቦታዎች መቀስቀሱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር በየነ ሞገስ ተናግረው ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት በሶማሌ ክልል ላይ በዋናነት ሸበሌ፣ ሊበንና ጃረር የሚባሉ ዞኖች ላይ ወረርሽኙ መከሰቱን እና በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ባሌ ላይ መዛመቱን ገልፀው ነበር።
በዓለም ዙሪያ በኩፍኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በ2018 ብቻ ከ140 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተደረገ ጥናት አመልክቷል። ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት መሆናቸውም ተነግሯል::