ኢትዮጵያ ነገ ዜና || 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ ያለው የሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር፤ ሜቴክ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ያለአግባብ በመውጣቱ ነው የሕዳሴው ግድብ ወደ ኋላ የተጓተተው ሲሉ መናገራቸው፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እጅግ የሚያስገርም ጉዳይ እንደሆነባቸው ተናገሩ፡፡
ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በህዳሴ ግንባታ የጫካ ምንጣራ ሥራ በብዙ ሚልዮን ብሮች ለብክነት እንዲጋለጡ በማድረግ ሒደት ላይ ዋናው ተዋናይ እንደነበሩና ከኢንጅነር ስመኘው በቀለ ላይም ጫና በማድረግ ሥራዎች ያለጨረታ ለዘመዶቻውና ከፓርቲያቸው ጋራ ንክኪ ላላቸው ወገኖች እንዲሰጥ ሲያደርጉ ነበር ያሉ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ውስጥ አዋቂ ምንጮች፤ “ደብረፂዮን ዛሬም ሜቴክ እና መሰል ተቋማት የሕዝብና የሀገር ሀብትን መመዝበራቸውን ሊከለከሉ አይገባም፣ የሚል ካፈርኩ አይመልሰኝ አስተያየታቸውን የሚያስተዛዝብ ነው” ብለዋል፡፡
“ሟች ኢንጅነር ስመኘው እኔ ወደ ትግራይ ከሄድኩ በኋላ መጥቶ ተወያይተን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ግደቡ 63 ፐርሰንት ደርሶ ስለነበር እንድታግዘኝ ብሎኝም ነበር” ሲሉዶክተር ደብረፂዮን ለጋዜጠኞች መናገራቸውን ያስታወሱት ምንጮች ደብረ ፂዮን ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ምንነት እንደማያውቅ ግለሰብ ሜቴክና ከዶክተሩ የቦርድ ሊቀ መንበርነት የሚመራው የህዳሴ ግድብ አስተዳደር ጋራ በዘረጉት ሚስጥራዊ ሰንሰለት የአገር ሀብትን ለብክነትና ለምዝበራ ማጋለጣቸውን ለመሸፋፈን መሞከራቸው ነው በማለት ይተቹታል፡፡