ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሕክምና ትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 209 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመረቀ።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተገኝተዋል።
ፕሮፌሰር ጣሰው እጩ ምሩቃኑ ላለፉት ሥድሥት ዓመታት የሕክምና ትምህርታቸውን በትጋት በመከታተል በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቃቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎች በቅንነት፣ በሀቀኝነት እና በታማኝነት አገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸውም የዮንቨርስቲው ፕሬዝዳንት መልዕክት አስተላልፈዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በበኩላቸው የሕክምና ሙያ ሓላፊነቱ የገዘፈ ጥንቃቄና ፅናት የሚሻ መሆኑን አስታውሰው እንደ ማንኛውም የሙያ መስክ አንዱ የስልጠና ምእራፍ ሲዘጋ ሌላው እየተከፈተ እንደሚሄድ ተናግረዋል።
ሙያው እየረቀቀ የሚሄድ፣ በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነና ዘመኑ ካፈራቸው ቴክኖሎጂዎች ጋር ራስን ማራመድ የሚጠይቅ በመሆኑ ተማሪዎች እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለማዳበር ጥረታቸውን ሳያቋርጡ መቀጠል እንዳለባቸውም መክረዋል::