ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አዲስ ተቀጣሪ ሠራተኞች የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለመቀላቀልና በተሻለ ፍጥነት ለማስቀጠል ዝግጁ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ ለአዲሶቹ ሠራተኞች ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ያወጣውን የሥራ ቅጥር ፈተና በላቀ ውጤት ያለፋ 8 ሺህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ልዩ ልዩ የሥራ መደቦች ላይ መመደባቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
ሠራተኞቹ ባለፋት ቀናት የቅድመ ሥራ ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የስልጠናው ማጠቃለያ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። በስልጠና የማጠቃለያ መድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እንጂነር ታከለ ኡማ፥ በአንድ ጊዜ 8 ሺህ ሠራተኛን በዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ወደ ሲቪል ሰርቪስ መቀላቀል አዲስ ባህል መሆኑን ጠቁመዋል።
ተቀጥሮ መሥራትንና ህዝብን ከማገልገል ጋር በተያያዘ የግል ተሞክሮአቸውን ያጋሩት ኢንጂነር ታከለ ኡማ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ የማድረግ የለውጥ ጉዞአችንን ተቀላቅላችሁ ሓላፊነታችሁን በአግባቡ በመወጣት ነዋሪያችንን አገልግሉ የሚል መልዕክት በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ አስተላልፈዋል።
“የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ለመቀላቀል እና በተሻለ ፍጥነት ለማስቀጠል ዝግጁ ሁኑ” በማለትም አሳስበዋል። አዲስ ተቀጣሪ ሠራተኞቹ ከፊታችን ማክሰኞ የካቲት 24 2012 ዓ.ም ጀምሮ በየተመደቡባቸው ሴክተሮች ፣ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች በመገኘት ሥራቸውን ይጀምራሉ ነው የተባለው።
ከ20 ሺህ በላይ የ2010 እና 2011 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች መካከል የመመዘኛ ፈተናውን ያለፉ 8 ሺህ ምሩቃን በዜሮ ዓመት ልምድ ነው በተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ ሴክተር መስፈሥሪያ ቤቶች የተመደቡት።
ታማኝ የዜና ምንጮቻችን እንደገለፁት ከሆነ ቀደም ሲል በመንግሥት ተቋማትና በየወረዳው በሥራ ላይ የተመደቡትም ሆነ አሁን ወደ ሥራ ይገባሉ የተባሉት ስምንት ሺኅ ወጣቶች ከ95 ፐርሰንት በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ያልሆኑና ከተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች የመጡ ሰዎች ናቸው::
ግልጽ የሆነ የተረኝነት ስሜት ይስተዋልበታል የሚባለው የታከለ ኡማ አስተዳደር ለይስሙላ ጥቂት የአዲስ አበባ ልጆችን ቀላቅሎ በብዛት ለኦሮሚያ ወጣቶች ሠፊ የሥራ ዕድል በመስጠት በተደጋጋሚ እየተተቸ ይገኛል::