የአፍሪካ አየር መንገዶች በአንድ ወር ብቻ 400 ሚሊዮን ዶላር ማጣታቸው ተረጋገጠ

የአፍሪካ አየር መንገዶች በአንድ ወር ብቻ 400 ሚሊዮን ዶላር ማጣታቸው ተረጋገጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ የካቲት ወር ላይ ብቻ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአፍሪካ አየር መንገዶች 400 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣታቸውን ዓለም ዐቀፉ የአየር ትራንስፖርት የበላይ ተቆጣጣሪ ገለጸ።

ምንም እንኳን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደሌሎቹ አህጉራት አፍሪካን ክፉኛ ባያጠቃም ያስከተለው ተጽእኖ ግን ቀላል የሚባል እንዳልሆነ እየተነገረ ነው። የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ የታንዛኒያ፣ የሞሪሺየስ፣ የማዳጋስካር፣ የሩዋንዳ፣ የሞሮኮ፣ የግብጽና የኬንያ አየር መንገዶች ወደ ቻይናና ከቻይና ወደ የአገራቸው የሚደረጉ ሁሉንም በረራዎች እንዲቋረጡ ማድረጋቸው ይታወቃል::

ዓለም ዐቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር እንደሚለውም ከኮሮናቫይረስ መስፋፋት ጋር በተያያዘ አየር መንገዶቹ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው አመልክቷል። ለዚህም እንደ ምክንያት የቀረበው አየር መንገዶቹ ወደ ቻይና የነበሯቸውን የበረራ መስመሮች በማቋረጣቸውና በረራዎችን በመሰረዛቸው እንደሆነ ተገልጿል።

የዓለም ዐቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት በተለይ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ላጋጠማቸው የአፍሪካ አየር መንገዶች የኮሮናቫይረስ ክስተት የገጠማቸውን ችግር የበለጠ የከፋ ያደርግባቸዋል ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ ወገኖች ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ ግፊት ቢደረግበትም እስካሁን ወደ ቻይና ከተሞች ጉዞ እያደረገ ይገኛል። ስለዚሁ ጉዳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም በሰጡት ምላሽ “አሁን ጊዜያዊ ችግር ስላጋጠማቸው በረራ ማቋረጥ በሞራልም በሥነ ምግባርም ተቀባይነት የለውም” በማለት የተከሰተውን ችግር ለመከላከልም “ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንጂ፤ በረራዎችን ማቋረጥ ግን ካሉ አማራጮች ውስጥ አይደለም” ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም::

እስካሁን ድረስ በግብጽ፣ በቱኒዚያ፣ በሞሮኮ፣ በአልጄሪያ፣ በናይጄሪያና በሴኔጋል በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው የተዘገበ ቢሆንም በየትኛውም የአፍሪላ አገር ውስጥ በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ አልተከሰተም ተብሏል።

የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስጠነቀቀው ደካማ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ያላቸው ድሃ አገራት ወረርሽኙን ለመቋቋም አቅም የላቸውም፤ ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ መሆኑ አሳሳቢ ነው ብሏል።በተያያዘ ዜና የኬንያ መንግሥት ከኮሮናቫይረስ የመስፋፋት ስጋት ጋር በተያያዘ ከሰሜናዊ የጣሊያን ሁለት ከተሞች የሚመጡ በረራዎች እንዲቋረጡ አዟል።

ኬንያ ይህንን እርምጃ የወሰደችው በአውሮፓ ውስጥ በርካታ ቫይረሱ የተገኘባቸው ታማሚዎች ካሉባት አገራት አንዷ ከሆነችው ጣሊያን የመጡ መንገደኞች አፍሪካ ውስጥ በበሽታው ተይዘው በመገኘታቸው ነው።

በቱኒዚያ፣ በሞሮኮና ናይጄሪያ ውስጥ በቫይረሱ ተይዘው የተገኙት ሰዎች ከጣሊያን የመጡ መሆናቸው ስጋት መፍጠሩን ተከትሎ ነው የኬንያ መንግሥት ናይሮቢ ከሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ጋር በመመካከር ነው የተወሰኑ በረራዎችን ከማቋረጡ ውሳኔ ላይ የደረሰው።

የኬንያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሙታሂ ካግዌ እንደተናገሩት ጣሊያን ውስጥ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ጣሊያን ውስጥ ቢያንስ 1800 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 52 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።

LEAVE A REPLY