ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ እንዳይገቡ አሥመራ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የታገዱት የኢትዮጵያውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ጉዳይን በማስመልከት የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኤርትራ መንግሥትን ማብራሪያ መጠየቋን ቫቲካን ኒውስ ዘግቧል።
የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ ያቀረበችው ለኤርትራው ብሔራዊ የሃይማኖት ጉዳዮች ቢሮ መሆኑ ተነግሯል። ለቢሮው የቀረበው የማብራሪያ ይሰጠን ደብዳቤ በኤርትራ የጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ አባ ተስፋጊዮርጊስ ክፍሎም የተፈረመ መሆኑን ከቫቲካን ኒውስ ዘገባ መረዳት ችለናል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ አሥመራ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የታገዱት ከሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ሁለት አባቶች ጋር ነበር። አባ ብርሃነ እየሱስና አብረዋቸው የነበሩት አባቶች ወደ አሥመራ ያመሩት፣ በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ኪዳነምህረት ደብር በሚደረግ ትልቅ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት እንደነበር ተገልጿል።
የሃይማኖት አባቶቹ ወደ አሥመራ እንዳይገቡ በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ መከልከላቸውን በማስመልከት ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ከታገዱት አባቶች አንዱ የነበሩት አባ ፍቅሬ ወልደትንሳኤ “ልዑኩ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሶ ማሟላት የሚገባውን ነገር ሁሉ አሟልቶ በተገቢው ሂደት አልፏል። መንገደኞች እንደደረሱ የሚሰጥ ቪዛም ለአንድ ወር ተብሎ ተሰጥቷል” ብለዋል።
አስፈላጊውን ፎርማሊቲ ጨራርሰውና ቪዛቸውን ተቀብለው ከአውሮፕላን ማረፊያው ሊወጡ ሲሉ ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የሚል ትዕዛዝ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መምጣቱ እንደተገለፀላቸውና ነገሮች በዚያ መልኩ እንደሄዱም አባ ፍቅሬ ወልደትንሳኤ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባቶች አሥመራ ከደረሱ በኋላ ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ በመከልከላቸው በአየር ማረፊያው ውስጥ ለበርካታ ሰዓታት መጉላላታቸው በጊዜው ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ ይታወሳል::