1.5 ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ የራስ ቅል በአፋር ተገኘ

1.5 ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ የራስ ቅል በአፋር ተገኘ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || “ኦልዶዋን” እና ” አሹሊያን” የተሰኙ የድንጋይ መሣሪያዎች ከሆሞ ኢሬክተስ የጭንቅላት ቅሪተ አካላት ጋር በአፋር ክልል የጎና መካነ ጥናት መገኘታቸው ተረጋገጠ።

የጭንቅላት መጠኑ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ከሚገኙትና ሆሞ ኢሬክተስ በመባል ከሚታወቁት የቅድመ ሰው ዝርያ አካላት አነስተኛ የሆነ የራስ ቅል ቅሬተ አካል ከተለያዩ የድንጋይ መሣሪያዎች ጋር ነው በጎና ፕሮጀክት መገኘቱ የተነገረው።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በጎና የተገኙት የራስ ቅሎች ሁለት ሲሆኑ ፤ ሆሞ ኢሬክተስ በመባል በሚታወቀው የቅድመ ሰው ዝርያ የሚካተቱ መሆናቸውን አመላክቷል። እነዚህ ቅሪተ አካላት ኦልዶዋን እና አሹሊያን ተብለው በሚጠሩት የድንጋይ ዘመን መሣሪያዎች ይጠቀሙ እንደነበር ተገልጿል።

የተገኘው የራስ ቅል የአንጎል መጠኑ (590 ሲሲ) ሲሆን ፤ ይህ ግኝት ከአሁን ቀደም በሆሞ ኢሬክተስ የድንጋይ መሣሪያ አጠቃቀም የነበረንን የእውቀት አድማስ በማስፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተሰምቷል ።

ግኝቱ ይፋ የተደረገው ስፔን በሚገኘው የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ በሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ስለሺ ሰማው እና በአሜሪካ በሳውዘርን ኮኔክቲከት ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር በሆኑት ዶክተር ማይክል ሮጀርስ በሚመራው የጎና መካነ ጥናት ፕሮጀክት መሆኑ ተሰምቷል ።

የመጀመሪያው በአቶ ኢብራሂም ሀቢብ የተገኘው ሙሉ የራስ ቅል 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዓመታት ዕድሜ አለው።በሁለተኛው ግኝት በፕሮፌሰር ኒኮላስ ቶዝ በከፊል የራስ ቅል የተገኘ ሲሆን ዕድሜው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓመት መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ግኝት ሆሞ ኢሬክተስ ሁለቱንም የድንጋይ መሣሪያ አይነቶች በአንድ ተመሳሳይ ጊዜ ሠርቶ ይጠቀም እንደነበር በጉልህ አመላካች መሆኑን ያሳያል ተብሎለታል። ቀደም  ሲል በአገራችን የተገኙት የሆሞ ኢሬክተስ ቅሪተ አካላት የሚታወቁት ከመካከለኛው አዋሽ (ዲካ)፣ መልካ ቁንጡሬና ከኮንሶ ብቻ ሲሆን፥ በጎናው ፕሮጀክት የተገኘው ሆሞ ኢሬክተስ ግኝት አዲስ እና አስፈላጊ ተጨማሪ መረጃን አበርክቷል::

የጎና የፓሌዎአንትሮሎጂ ጥናት ፕሮጀክት ባለፉት 30 ዓመታት የምርምር ሥራው በዓለም እጅግ ጥንታዊና 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠሩ የድንጋይ መሣሪያዎችን እንዲሁም 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠረውን አርዲፒቲከስ ራሚደስ የተባለውን ጥንታዊ ሰው ቅሪተ አካል በማግኘት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ በማሳተም ጉልህ ስፍራ ይዟል።

LEAVE A REPLY