ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሳዑዲ አረቢያ የልዑል አልጋወራሹን ሞሐመድ ቢን ሳልማን ታናሽ ወንድምን ጨምሮ ሦስት የአገሪቱ ልዑላንን ማሰሯን ኒዮርክ ታይምስና ዋል ስትሪት ጆርናል በዘገበቸው ይፋ አድርገዋል።
ልዑላኑ የታሰሩት ትናንት አርብ ማለዳ መሆኑ ተረጋግጧል:: ከታሰሩት ልዑላን መካከል ሁለቱ በሳዑዲ ዘውዳዊ ግዛት ውስጥ ከፍተኛ ተፅእኖ ያላቸው ሲሆኑ፤ ለልዑላኑ መታሰር ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ነገሩ ከልዑል አልጋወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመነገር ላይ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 በልዑል አልጋወራሽ ቢን ሳልማን ቀጭን ትዕዛዝ ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ባለሀብት ሼክ ሞሐመድ አሊ አላሙዲንን ጨምሮ በርካታ የሳዑዲ ንጉሣዊያን ቤተሰብ አባላት የሆኑ ታላላቅ ሰዎች፣ ሚኒስትሮችና ባለሀብቶች በሪያዱ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።
ሞሐመድ ቢን ሳልማን በ2016 በአባታቸው በሳዑዲው ንጉሥ፤ ልዑል አልጋወራሽ ተብለው መሾማቸውን ተከትሎ የሳዑዲ ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል። ሳዑዲ ያሰረቻቸው ልዑላን የልዑል አልጋወራሽ ቢን ሳልማን ታናሽ ወንድም የሆኑት ልዑል አህመድ ቢን አብዱልአዚዝ፣ የቀድሞ ልዑል አልጋወራሽ ሞሐመድ ቢን ናይፍ እና ልዑል ናዋፍ ቢን ናይፍ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ሞሐመድ ቢን ናይፍ በልዑል ቢን ሳልማን ትዕዛዝ 2017 ላይ በቤት ውስጥ የቁም እስረኛ እስከተደረጉበት ጊዜ ድረስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። የዋልስትሪት ዘገባ እንደሚያመለክተው ጥቁር ልብስ የለበሱና የፊት ጭምብል ያደረጉ ጠባቂዎች ወደ ልዑላኑ መኖሪያ ቤት በመሄድ ቤታቸውን በርብረዋል።
በ2016 እጅግ ወግ አጥባቂ በሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ቃል የገቡት ሞሐመድ ቢን ሳልማን በጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ ዓለም አቀፍ አድናቆት ተችሯቸው እንደነበር አይዘነጋም።