ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ ናዲን ዶሪስ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተሰማ። ሚኒስትሯ በዩኬ በቫይረሱ የተያዙ የመጀመሪያዋ የሕዝብ እንደራሴ ሲሆኑ ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ አንደወሰዱና ራሳቸውንም ከሌሎች አግልለው መቀመጣቸውን አስታውቀዋል።
በዮኬ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ ስድስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን 382 ደግሞ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተሰምቷል። በቅርቡ በቫይረሱ ከተያዙና ከሞቱ ግለሰቦች መካከል የ80 ዓመት አዛውንት የሚገኙበት ሲሆን ግለሰቡ ሌሎች የጤና ችግሮች እንደነበሩባቸው መረጃውች ይጠቁማሉ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ፣ ናዲን ዶሪስ ያገኟቸው ሰዎች በአጠቃላይ ክትትል እየተደረገባቸው ነው። ሚኒስትሯ የቫይረሱን ምልክት ማሳየት የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ነበር:: በዚያው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ባዘጋጁት ሥነ ሥርዓት ላይ ተሳትፈዋል።
ከአርብ ዕለት ጀምሮ ግን ራሳቸውን ከሰው አግልለው መቀመጣቸው ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ያድርጉ አያድርጉ የታወቀ ነገር የለም። ከሚኒስትሯ ጋር ግንኙነት የነበራቸው የጤና ሚኒስትር መሥሪያቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በአጠቃላይ ምርመራ እየተደረገላቸው ይገኛል።