ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሃይማኖት ሰባኪ ነው። የሰባኪ ስራ ደግሞ ሃይማኖቱን ማስፋፋት ነው።ሁሉም ሰው የራሱ ሃይማኖት ትክክለኛ ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ የሃይማኖቱን አስተምሮ ለነፍሳት ሁሉ ማዳረስ ይፈልጋል። ሃይማኖትን የማስፋፋትን ስራ እንደ ዳንኤል ክብረት ያሉ በዓለማዊው ግንዛቤም በመንፈሳዊው እውቀትም ሙክክ ብለው የበሰሉ ሰዎች ሲሰሩት ዓላማው መንፈሳዊና መልካም ነው።
ይህ መልካም መንፈሳዊ ዓላማ “እኔ የያዝኩት መንፈሳዊ መንገድ የመዳኛው መንገድ በመሆኑ ወንድም እህቶቼ እኔ ያገኘሁትን እድል ያገኙ ዘንድ የሃይማኖቴን ወንጌል (የምስራች) ላካፍላቸው” የሚል ነው። ይህን መንፈሳዊ ዓላማ ማሳኪያው ስብከት ነው። ስብከት ደግሞ የሚፈልገው ፍቅርን፣የሰዎችን በጎ ፈቃድና የሰባኪውን ጊዜ እና እውቀት ብቻ ነው። ሰው ሃይማኖቱን ሲያስፋፋ ሊያደርግ የሚችለው ህጋዊም መንፈሳዊም ተቀባይነት ያለው መንገድ ይህ ነው። ዳንኤል ክብረትም ከዚህ የተለየ ነገር አድርጎ አየሁት የሚል የለም! ዳንኤል “ያላመነውን አንገቱን በሰይፍ ቁረጠው” ሲል ሰማሁ የሚል አለ?!
ሰባኪን የሚያስወቅሰው፣ በህግም የሚያስጠይቀው እንዲህ ባለው የሃይል መንገድ ከሄደ ነው። በሃይል ሃይማኖት ማስፋፋት እኔ በደንብ በማውቀው የክርስትና ሃይማኖት ውገዝ ነው። በሌሎች ሃይማኖቶችም እንደዛው ይመስለኛል።
ዳንኤል ክብረት ትናንት በፓርላማው እንደ ትልቅ ጉዳይ የተነሳበት ነገር ሃይማኖታችንን ለማስፋፋት አልሰራንም ሲል የተናገረው ንግግር መሰለኝ። ይህን ነገር እንደ ትልቅ ወንጀል አንስቶ ሲያወራ የነበረው ሰውዬ አሁን ምን እንደሆነ ባላውቅም የሆነ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መምህር ነበረ። የዩኒቨርሲቲ መምህር ደግሞ የመንደርደሪያን (premises) እና መደምደሚያን (Conclusion) ጥብቅ ትስስር የሚያውቅ ነው። ዳንኤልን ሃይማኖቶችን ሁሉ እኩል ያይም ብሎ የደመደመበት መንደርሪያ (premises) ምን እንደሆነ የጠየቀውም የለም እሱም ስለመደምደሚያው እንጅ ስለመንደርደሪያው የሚጨንቀው አይመስልም። መደምደሚያ መንደርደሪያ፣ አሳማኝ ማስረጃ እንደሚያስፈልገው ማንም በፓርላማው ያለ ሰው የተጨነቀበት አይመስልም። በመቀጠል የተናገሩት በየድንኳኑ የሚያለቅሱት የህወሃት አባላት ችግራቸው ግልፅ ስለሆነ ወደነሱ ንግግር አልገባም።
ለማንኛውም ዳንኤል ሃይማኖቶችን እኩል አያይም ያሰኘው ስለ ራሱ ሃይማኖት መስፋፋት በሚያወራበት ቪዲዮ ስለ ባውላ ሃይማኖት ወቅታዊ አቋም፣ ስለ ፕሮቴስታንት ሃይማኖት የበለጠ መስፋት፣ ስለተጨማሪ መስጊዶች መገንባት፣ ስለ ሂንዱ ሃይማኖት በኢትዮጵያ አለመንሰራፋትም አብሮ ማውራት ነበረበት ተብሎ ነው?