በረከት ስምኦን ፍርድ በፍጥነት እንዲሰጣቸው ዛሬ በችሎት ተማጸኑ

በረከት ስምኦን ፍርድ በፍጥነት እንዲሰጣቸው ዛሬ በችሎት ተማጸኑ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ በረከት ስምኦን ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ክስ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዚያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠረ።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት በዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሾቹ መካከል የነበረው ክርክር መጠናቀቁን ገልጿል። ስለሆነም ክሱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያለውን የከሳሽና የተከሳሾች የቃልና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ለሚያዚያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን በባሕርዳር የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገኝተው የነበሩ የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ገልጸውልናል ።

በእነ በረከት ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቃል እና የሰነድ ማስረጃዎች፤ እንዲሁም በከሳሾች የቀረቡ የሰነድ እና የቃል ማስረጃዎችን ለመመርመር ብዙ ጊዜ እንደሚስፈልገው ፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

አቶ በረከት ባለፉት ጥቂት ሣምንታት የጤናቸው ኹኔታ አሳሳቢ እንደሆነና በጸና ስለመታመማቸው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲገለጽ ነበረ።

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ አቶ በረከት  ስምኦን ካለባቸው የጤና ችግር አንጻር የፍርድ ውሳኔ በቀጠሮ ቀን እንዲታይላቸው ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን ለማፋጠን ምርመራውን በተገቢው ሁኔታ እንደሚመለከተው ምላሽ ሰጥቷል።

LEAVE A REPLY