የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለህዳሴው ግድብ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን አሉ

የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለህዳሴው ግድብ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ የቀድሞው ሠራዊት የልማትና የድጋፍ ማህበር ግብጽ ታላቁን የህዳሴ ግድብ አስመልክታ የምታሰማውን ድንፋታ አጣጥሎ ፤ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ገለጸ::

ማኅበሩ በራስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ግብጽና የአረብ ሊግ ያሳለፉትን ውሳኔ ያጣጣለ ሲሆን፤ ግድቡን አስመልክቶ መንግሥት ለሚያደርገው ጥሪ ከጐኑ እንደሚሰለፉም የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሀምሳ ዓለቃ ብርሃኑ አማረ አስታውቀዋል፡፡

ሠራዊቱ ማኅበሩን በሲቪል ማኅበርነት ያቋቋመ ቢሆንም በአገር ላይ ለሚቃጣ ማንኛውም ጉዳይ የውትድርና ሙያው በውስጡ ያለ በመሆኑ ለየትኛውም ያገር ጥሪ ፈጥኖ እንደሚደርስ ነው የገለጸው፡፡

ማኅበሩ በአየር ሀይል፣ በባህር ሀይል በመደበኛና በሚሊሺያ በአጠቃላይ በአምስቱም ዘርፍ አገሩን ሲያስከብር የነበረና ኤርትራን ጨምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በ200 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የተዋቀረ ከ1. ሚ በላይ አባላትን ያቀፈ መሆኑን የገለፁት የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ አባል መቶ አለቃ ታሪኩ በቀለ፤  “ሠራዊት አያረጅም፤ በጦር ግንባር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በመረጃ ትንተናና በማማከር በኩል አገሩን የሚያገለግል የ18 ዓመት ወጣት ወኔ ያለው ሀይል ነው” ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ብቻ ተጠቅማ ግብፃዊያን ወንድሞቻችን በርሃብ ይለቁ አንልም፤ ነገር ግን የውሃውም የአፈሩም ባለቤት ሆነን ሳለ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸውና አቅም ባለመፍቀዱ ሳንጠቀም ቆይተናል፤ አሁን በራስ አቅም ግንባታ ተጀምሯል፤ ተጠናቅቆ ስራ እስኪጀምር የሚጠበቅብንን እናደርጋለን ” ብለዋል የቀድሞ ሠራዊት አባላት፡፡

ኢትዮጵያ የሀገርን ጥቅም በማይጐዳ መልኩ የድርድር ጥሪ ከቀረበላት መደራደርና በሰላም መፍታት ለሁሉም ወገን አዋጪ መሆኑን የገለፁት የቀድሞ ሰራዊት አባላት ያ ካልሆነ ግን ለግብጽ ድንፋታ ምላሽ በመስጠቱ በኩል ግንባር ቀደም ተሰላፊ የሚሆን ሠራዊት በመላ አገሪቱ እንዳለም በመግለጫው ተገልጿል፡፡

ሠራዊቱ በአሁኑ ሰዐት ከ30 ዓመት ጭቆናና አንገት መድፋት ለውጡ ታድጐት ለልማት ዝግጁ እንደሆነ የገለፁት የማህበሩ ሓላፊዎች ፤ በቀጣይ ሁለት ትልልቅ የልማት ተቋማትን ለማቋቋም በሂደት ላይ ሲሆን ተቋማቱ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ባንክና የጥበቃ ካምፓኒ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ በሚዛን ሻኮ አካባቢ የዶሮና የከብት እርባታና ማደለቢያዎችን ለማቋቋም እንዲሁም በግብርናውም አመርቂ ሥራ ለመሥራት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ይፋ አድርገዋል፡፡

በቀጣይም ሰራዊቱ ምክር ቤት በማቋቋም በሂደት ላይ ሲሆን ሁለት ጥያቄዎችን ለመንግሥት ማቅረቡን የገለፁት ሓላፊዎቹ ጥያቄዎቹም የጡረታና የህክምና ጥያቄዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጪው ክረምት በሚደረገው አገር ዐቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሠራዊቱ ስላለው አስተያየት ተጠይቀው ሓላፊዎቹ ሲመልሱ “ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ፤ ምርጫ ቦርድ በፀጥታ፣ በምርጫ ታዛቢነትም ሆነ በጥበቃ ሥራ ሊገለገልብን ይችላል” ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY