ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ውብሸት ኦቶሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በተለያየ ሥፍራዎች በእምነታቸው የተነሳ ብቻ ጥቃት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋም ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ገለጹ።
ማህበረ ቅዱሳን ጉዳት በደረሰባቸውና መንቀሳቀስ በቻለባቸው አካባቢዎች የደረሰው ጥቃት ምንድን ነው? ምእመናን ምን ዓይነት ጉዳት ደረሰባቸው ? ምን ቢሠራ እነዚህን ሰዎች ማቋቋም ይቻላል? የሚለው መጠናቱን ዋና ጸሐፊው አብራርተዋል።
ማኅበሩ መንቀሳቀስና ማጥናት በቻለባቸው ሥፍራዎች ካገኘው መረጃ በመነሳት ይፋ እንዳደረገው የተለያየ ጉዳት ያስተናገዱ ሰዎችን ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ከጴጥሮሳውያን የቤተክርስትያን መብትና ክብር አስጠባቂ ኅብረት፣ እንዲሁም ከዳንዲ አቦቲ ማኅበር ጋር በጋራ በመሆን ማኅበረ ቅዱሳን በጃንሜዳ የገቢ ማሰባሰቢያውን እንደሚያደርግ ሓላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች የተደረጉ የለውጥ ሂደቶች ቤተክርስቲያኒቷ እና በአማኞቿ ላይ የተለያየ ጥቃት ደርሷል ያሉት ዋና ጸሐፊው ለዚህም ምክንያቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚነገሩ የሀሰት ትርክቶች መሆናቸውን አስቀምጠዋል:: ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቃጠሉና ሙሉ በሙሉ የወደሙ ከ20 በላይ ፣ ከአስር የማያንሱ ደግሞ የተለያየ መጠን ጉዳት የደረሰባቸው አብያተክርስቲያኖች መኖራቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
ከአብያተ ቤተክርስትያናቱ በተጨማሪ ምዕመናኑ ላይ የተለያየ ጉዳት መድረሱን የገለጹት የማህበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ፣ ከሞቱት ባሻገር ቤት ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው፣ አካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ ወደተለያየ አካባቢ የተፈናቀሉ ምዕመናን በርካታ እንደሆኑም ይፋ አድርገዋል።
የወደሙባቸው አገልግሎት መስጫ ተቋማትና ቤታቸው የሚሠራላቸው 417 ሰዎች፣ ሌሎች በተለያየ መንገድ ድጋፍ የሚደረግላቸው ደግሞ 1ሺህ 700 ሰዎች መሆናቸውን ያመላከቱት አቶ ውብሸት ፤ ንብረቶቹን ብቻ መልሶ ለመተካት 400 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ መገመቱን ገልጸው፤ 200ሚሊዮኑ ለሕክምናና ለስነልቦና ድጋፍ እንደሚውል አስረድተዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስትያናት በምዕመናኑ ድጋፍ እየታነፁ መሆኑን እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ግን አስታዋሽ አጥተው መቸገራቸውን ያስታወሱት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ፤ እስካሁን የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ለመማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የፊታችን መጋቢት 27 ቀን በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ፕሮግራም መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ በትንሹ 30 ሺህ የእምነቱ ተከታዮች እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን ከአገር ውጪ የሚኖሩ በዕለቱ በማኅበሩ ድረ ገፅ በቀጥታ በመግባት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ሥራ እንዲሠራ ከጠቅላይ ቤተክህነት በተጻፈ ደብዳቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጠይቆ ፈቃድ ማግኘቱን ጨምረው ገልፀዋል።
አቶ ውብሸት ማኅበራቸው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንደሚያወግዙ በመጥቀስ በቤተክርስቲያኒቷ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ግን ተገቢውን ትኩረት አላገኙም ሲሉ መንግሥትን ወቅሰዋል::