ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቀሌና ላልይበላን ጨምሮ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍሎች ዛሬ ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎችን ባጋጠመው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት መሰረዙን ይፋ አደረገ።
በተመሳሳይ ወደ ጎንደር፣ አክሱምና ሽሬ ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎችም ዛሬ ጠዋት በነበረው አመቺ ያልሆነ የአየር ሁኔታ ሳቢያ መስተጓጎሉን ገልጿል። በዛሬው ዕለት የተሰረዙትን በረራዎች ያለው የአየር ሁኔታ መሻሻሉን በተመለከተ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የሚገኝን መረጃ መሰረት በማድረግ እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑን የአፍሪካ ኩራት የሆነው አየር መንገዳችን አስታውቋል።
ነከሰዓት በኋላ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በረራዎችን ያስተጓጎለው የአየር ሁኔታጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥም ሊቀጥል እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።
በተያያዘ ዜና ከአርብ ከሰዓት ጀምሮ ቅዳሜ ዕለትም የባህር ዳር ከተማ ሰማይ በአቧራ ጭጋግ ተሸፍኖ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ክስተቱን በተመለከተ የምዕራብ አማራ የሜቲዮሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የትንተናና ትንበያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጥላሁን ውቡ”ጠንካራ የአቧራ ጭጋግ ተከስቷል።” ብለዋል:: ይህ የአቧራ ጭጋግ የሚከሰተው በደረቅ አካባቢዎች የሚከሰትን አውሎ ነፋስ ተከትሎ ነው ያሉት ባለሙያው፤ በባህር ዳር ላይ የታየው የአቧራ አውሎ ነፋስ ሱዳን ላይ በተከሰተ ዝቅተኛ የአየር ግፊት ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
የአቧራ ጭጋጉ የተከሰተው በባህር ዳር ከተማ ብቻ አለመሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው ጎንደር ላይም መታየቱን ተናግረዋል። ክስተቱ ብዙ ጊዜ ለረዥም ሰዐት አይቆይም የሚሉት አቶ ጥላሁን ቶሎ ሊጠፋ እንደሚችል ገልጸው ነገር ግን በእንዲህ ዓይነት የአየር ሁኔታ አውሮፕላኖች ለመነሳትም ሆነ ለማረፍ እይታን ስለሚጋርድ ለበረራ አስቸጋሪ እንደሚሆን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ ግን በረራዎች ከተስተጓጎሉባቸው ከተሞች ውስጥ የአቧራ ጭጋጉ የተከሰተባት የባህር ዳር ከተማ የለችበትም።
እንዲህ አይነት አቧራ ጭጋግ የመተንፈሻ አካል ችግር በተለይ አስም ላለባቸው ሰዎች አስቸጋሪ እንደሚሆን ፣እንዲሁም ክስተቱ የማጅራት ገትር በሽታ መንስዔም ሊሆን እንደሚችል ሓላፊው አስረድተዋል።