ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮሮና ቫይረስ በተደረገላቸው ምርመራ ከበሽታው ነጻ ሆነው እንደተገኙ የጽህፈት ቤታቸው ዶክተር ገለጹ።
ሾን ኮንሊይ ከሰዓታት በፊት ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት “ነጻ መሆናቸውን የሚያመለክተውን የፕሬዝዳንቱን የምርመራ ውጤት ቅዳሜ ምሽት ተቀብያለሁ” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምርመራ የተደረገላቸው ከመካከላቸው የተወሰኑት የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ከብራዚል ልኡካን ጋር ፍሎሪዳ ውስጥ ከተገናኙ በኋላ መሆኑ ታውቋል።
በሽታው ከተገኘባቸው የልኡኩ አባላት መካከል የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ረዳት የሆኑ ግለሰብም ይገኙበታል ተብሏል። “ትራምፕ ከብራዚል የልኡካን ቡድን ጋር ከነበራቸው የእራት ፕሮግራም ከሳምንት በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ከበሽታውና ከበሽታው ምክልቶች ነጻ ሆነው ተገኝተዋል” ሲሉ ሾን ኮንሊይ አረጋግጠዋል።
የ73 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከልኡካን ቡድኑ ጋር ከተገናኙ በኋላ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት አልታየብኝም በማለት እራሳቸውን ከሌሎች ለይተው አላቆዩም ነበር። ነገር ግን ዋይት ሐውስ ውስጥ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቀረበላቸውን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ተከትሎ ምርመራ እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር። የአሜሪካ መንግሥት እንደሚያዘው ከሆነ በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ለ14 ቀናት እራሳቸውን ለይተው በቤታቸው ውስጥ መቆየት ይጠበቅባቸዋል።
አሜሪካ ውስጥ እስካሁን ከ2,700 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ 54 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል። አርብ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሽታውን ለመዋጋት የሚያስችል የ50 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመፍቀድ የሚያስችላቸውን ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጋቸው ይታወሳል።
በዓለም ዙሪያ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት በተጨማሪ ሌሎች መሪዎችና ፖለቲከኞችም በበሽታው ተይዘዋል የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ ምርመራና እራስን ለይቶ የማቆየት እርምጃ እየወሰዱ ናቸው::