በአዲስ አበባ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል ዋጋ ንሯል፤   በፈርማሲዎች ሊገኝ አልቻለም

በአዲስ አበባ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል ዋጋ ንሯል፤   በፈርማሲዎች ሊገኝ አልቻለም

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አዲስ አበባ  ከተማ ውስጥ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ገንዘብ ሲሸጥ እንደነበረና በመደብሮች ውስጥ ማግኘት እንዳልቻሉ ነዋሪዎች ገለጹ።

አርብ ዕለት አዲስ አበባ ላይ የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት የመጀመሪያው የተረጋገጠ የኮሮናቫይረስ ታማሚ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተገኘ በኋላ ስጋት የገባቸው ሰዎች የፊት ጭንብልና ፈሳሽ የእጅ ማጽጃ ውህዶችን በመግዛት ላይ ናቸው። ቢቢሲ ያናገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳሉት በሽታው አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ሊከላከለው ይችላል የተባሉ ነገሮችን እየገዙ መሆናቸውን ነገር ግን የጭንብሎቹና ፈሳሽ የንጽህና መጠበቂያዎች [ሳኒታይዘር] እንደልብ እንደማይገኙ ከተገኙም ዋጋቸው በሚያስደነግጥ ሁኔታ መናሩን አስረድተዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የመድኃኒት መደብሮችም የፊት ጭንብልና ሳኒታይዘር እንደሌላቸው በሚለጥፉት ማስታወቂያም ሆነ በተጠየቁ ጊዜ የሚሰጡት ምላሽ እንደሆነ  በግልጽ መታየት የጀመረው ከቅዳሜ ማለዳ አንስቶ ነበር።

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይም በርካቶች የፊት ጭንብል ስለመጥፋቱና ስለመወደዱ ገጠማቸውን በጽሁፍና በምስል እያሰፈሩ ነው፤ ጭንብሉ ያለባቸው ፋርማሲዎች ረዘም ያሉ ሰልፎች የታዩ ሲሆን ውስን ቁጥር ያላቸውን መሸፈኛዎችን በመደበኛው ዋጋ ሲሸጡ እንደነበርም በመነገር ላይ ነው።

ቢቢሲ ያናገራቸው በአዲስ አበባ ያሉ ሁለት የመድሃኒት መደብሮች የፊት መሸፈኛ ጭምብል እንደጨረሱና ሲሸጡ የነበረውም ቀደም ሲል በነበረው ዋጋ እንደሆነ ገልጸዋል። የከተማዋ ባለስልጣናትም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ተፈላጊ በሆኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሚሸጡ የንገድ ተቋማት ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን አመልክተው፤ ኅብረተሰቡም ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

በርካታ ሰዎች በሽታውን ሊከላከል ይችላል በማለት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ለመግዛት ወደ መድኃኒት መደብሮች ቢሄዱም ለማግኘት እንደተቸገሩ ተናግረዋል።

“ሰው ሁሉ እየገዛ በመሆኑ ለልጆቼም ሆነ ለእራሴ የሚሆን ማስክ ለመግዛት ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በየደረስኩበት ቦታ ያሉ ፋርማሲዎችን ብጠይቅም ላገኝ አልቻልኩም” ያሉት የሁለት ልጆች እናትና አዲስ አበባ ውስጥ አብነት የሚባለው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ መብራት አስቻለ አንዷ ናቸው።  ወይዘሮ መብራት ጎረቤቶቻቸው ጭንብሉን እስከ 200 ብር በሚደርስ ዋጋ ከሰዎች ላይ መግዛታቸውን ቢሰሙም ነገር ግን ይህን ያህል ገንዘብ በማውጣት ለቤተሰባቸው መግዛት ከባድ ስለሆነባቸው እንደተዉት ገልጸዋል።

ከፊት መሸፈኛ ጭምብሎች በተጨማሪ የእጅ ማጽጃ  ፈሳሾችም ዋጋቸው የጨመረ ሲሆን ፤ ተህዋሲያንን ያጠፋሉ ተብለው የሚነገርላቸው ሳሙናዎችም ተፈላጊነታቸው ጨምሯል። ዋጋቸውም በዚያው ልክ መጨመሩን ነዋሪዎች  ተናግረዋል።

የከተማው መስተዳደርም “የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ተጠቂ ተገኝቷል” የሚለው መረጃ ከወጣ በኋላ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ይፋ አድርጓል::

 

LEAVE A REPLY