ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክትር ቶላ በሪሶ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት እራሳቸውን ለይተው በአንድ ክፍል ለብቻቸው መቀመጣቸውን ተናገሩ።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ተብሎ ይፋ ከተደረገውና ጃይካ የሚባለው በትምህርት ላይ ከሚሰራው የተራድኦ ድርጀት ባልደረባ ከሆነው ጃፓናዊ ጋር በሥራ ምክንያት መገናኘታቸው እራሳቸውን ለተወሰኑ ቀናት ለይተው እንዲያቆዩ ያደረጋቸው ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው አስታውቀዋል።
ጃፓናዊው ከዶክትር ቶላ ጋር በተገናኘበት በዚያን ጊዜ “ገና ከውጪ አገር መምጣቱ ስለነበር ምንም አይነት የበሽታው ምልክት አይታይበትም ነበር” በማለት ከእርሱ ጋርም አንድ ኢትዮጵያዊ አብሮት እንደነበረም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ ጃፓናዊ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በአርሲ ዞን ሁለት ትምርት ቤቶችን ጎብኝቶ እንደነበረ የሚናገሩት ኃላፊው እሱ በሄደባቸው ቦታዎች አብረተውት የነበሩ ሰዎች ለብቻም እራሳቸውን ለይተው ክትትል እተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ጃፓናዊው የኮሮናቫይረስ ምልክት የታየበት ሰኞ ዕለት ሲሆን በሽታው እንዳለት ተረጋግጦ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ የኮሮናቫይረስ ታማሚ መሆኑ የተገለጸው ግን አርብ ዕለት ነበር። ይህን ተከትሎ ዶክትር ቶላ ከዚህ ግለሰብ ጋር ከተገናኙ ዐስር ቀናት እንዳለፉ ቢሆንም አሁን ለብቻቸው ተለይተው እንዲቆዩና ክትትል እንዲደረግላቸው የተነገራቸው አርብ ዕለት ነበር።
ዶክትሩ ከጃፓናዊው ጋር በመገናኘታቸው ከተፈጠረው ጥርጣሬ ውጪ እስካሁን የተለየ ምልክት እንዳልታየባቸው ተናግረዋል።የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊው ለዐስራ አራት ቀናት ከቤተሰባቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሳይገናኙ ለብቻቸው እንዲቆዩም ተነግሯቸው ይህንም እያደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኮሮናቫይረስ በወረርሽኝ ዓለም ዙሪያ ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ስድስት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ሲሞቱ፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው ደግሞ 155 ሺህ በላይ ደርሷል።