እውን ኮሮና የመጣው ፈጣሪ “ኃያላኖችን” ሊቀጣ ነው? || ታምሩ ገዳ

እውን ኮሮና የመጣው ፈጣሪ “ኃያላኖችን” ሊቀጣ ነው? || ታምሩ ገዳ

ለአለማችን የዘመኑ ታላቅ ስጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ዙሪያ በአንዳንድ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በኩል የሚሰጡት አስተያየቶች አንዳንዶቹ በእጅጉ ያሳዝናሉ ሌሎቹም እንዲሁ ይገርማሉ።

የዙምባብዌ የመከላከያ ሚኒስተሯ ኦፓኣህ ሙቺንግሪይ ቅዳሜ እለት በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት “እነዚያ በእኛ ላይ የኢኮኖሚያዊ ማእቀብ የጣሉ ኃያላን አገሮች ዛሬ አብዛኞቹ ማእቀብ ትጥሎባቸው በቤቶቻቸው ውስጥ ታሽገዋል።

በኢኮኖሚ ማእቀብ ሳቢያ እኛን እንዳስለቀሱን ሁሉ እነርሱም እያለቀሱ ይገኛሉ ። ፕ/ት ዶናል ትራምፕም ቢሆኑ ዘለአለማዊ እና ፈጣሪ አለመሆናቸውን ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል። እነዚያ እኛን በማእቀብ ያጨናነቁን አገራት ዛሬ እነርሱ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ሊጨናነቁ ወረፋው አሁን ለእናንተው ነው” ብለዋል።

የዙምባቡዌ ከፍተኛ ሹሟ አስተያየትን በማህበራዊ መረቦች አማካኝነት ያነበቡ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ቅሬታቸውን የገለጹ ሲሆን አንዳንዶች በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ መነሻው አገር የዙምባብዌ የቅርብ ወዳጅ ከሆነችው ከቻይና ምድር መሆኑን እንኳን ያላወቁት የመከላከያ ሚኒስትሯ ኦፓኦዎ “ስልጣናቸውን በአስቸኳይ ይልቀቁ ” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

በመከላከያ ሚኒስተሯ አስተያየት የተቆጡት የቀድሞው ም/ል ሚኒስተር ጎድፍሬይ ጋንዳዋ በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ ሚኒስተሯን “የአብዛኛው የዙምባብዌ ህዝብን የማይወክሉ፣መሀይም ባለስልጣን ” በማለት የወረፏቸው ሲሆን በኮሮና ቫይረስ ለተጠቁ ወገኖችም በዙምባቡዌ ህዝብ ስም ፈጣሪ ምህረቱን እንዲሰጣቸው ተመኝተዋል።

የኮሮና ቫይረስ በሽታ ተፈጥሮአዊ በሽታ መሆኑ ተረስቶ የፖለቲካ ጡንቻ መፈታተኛ የሆነበት ወቅት ላይ የተደረስ ሲሆን የአለማችን ግዙፉን ኢኮኖሚ የሚዘውሩት አሜሪካ እና ቻይናም በወረርሽኙ ዙሪያ ሰሞኑን የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው ተስተውለዋል ።

የፕ/ት ትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣናት በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ በሚሰጧቸው አስተያየቶች “የቻይናው ኮሮና ፣የቻይናው በሽታ” የሚሉ አግላይ ቃላት መጠቀሙ ፣ቻይናን ከበሽታው ጋር በቀጥታ ማገናኘቱ ያበሳጫቸው የቻይና ባለስልጣናት በተለይ ደግሞ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር አፈቀላጤ የሆኑት ዛአኦ ልቦን ከሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ በላይ ለሆኑት የትዊተር ተከታዮቻቸው እና በህዝባቸው ዘንድ “የኮሮና ቫይረስ በመጀመሪያ የተከሰተው በአሜሪካ ውስጥ ሲሆን ወደ ቻይናው ውሃን ግዛትም የተዛመተው በአንድ አሜሪካ ወታደር አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም ” የሚል መላምት ዘገባን ያናፈሰ ድህረ ገጽን በመጥቀስ ወሬው በበርካታ የቻይና ማህበራዊ ድህረ ገጽ ተከታዮች ዘንድ አመኔታ እንዲኖረው ጥረት አድርገዋል ሲል ብሉምበርግ የዜና አገልግሎት አስነብቧል ።

LEAVE A REPLY