ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋም ተዘጋ:: በነፃነት ታጋይዋ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው ምርጫ ቦርድ የተዘጋበት ምክንያት በኮረና ቫይረስ የተጠረጠረ የውጭ ዜጋ ከባድ የበሽታ ምልክት ታይቶበት ለሕክምና መሄዱን ተከትሎ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።
በ UNDP – በኩል ተመድቦ እየሠራ የሚገኘው ደቡብ አፍሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው ወደ ኢትዮጵያ ከገባ አንድ ወር የሞላው መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፌስ ቡክ ገጹ ይፋ አድርጓል። ጥርጣሬውን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ጥንቃቄ ለመውሰድ ዛሬ ተቋሙ እንደተዘጋ፤ ሠራተኞቹም ሥራ እንዳልገቡ ምንጮቻችን አረጋግጠውልናል።
ግለሰቡ ምልክት እየታየባቸው ምንም አይነት ምርመራ ሳይደረግላቸው መቆየቱን ቦርዱ የገለጸ ሲሆን ምርመራ ሳይደረግለት የቆዩበትን ምክንያትም ሆነ መንግስት ለቦርዱ ጥቆማ ትኩረት ያለመስጠቱን አስመልክቶ የሰጠው ማብራሪያ የለም።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ማስታወቂያ የውጭ ዜጋው ከአንድ ወር በፊት ወደ አገር ውስጥ የገባ ሲሆን ቦርዱም ምልክቶቹ ከታዩበት ጊዜ አንስቶ ምርመራ እንዲደረግለት ጠይቆ ምርመራው እንዲካሄድ እየጠበቀ ይገኛል፡፡ ከማለቱም በተጨማሪ ምርመራው ተከናውኖ ውጤቱ ሲታወቅ ተጨማሪ መረጃ የምንሰጥ ይሆናል፡፡ የሚል ሲሆን ምርጫ ቦርድን ያህል ትልቅ ተቋም ምርመራው እንዲካሄድለት ጠይቆ አፋጣኝ ምላሽ አለማግኘቱ አሳዛኝ መሆኑን የጠቆሙ አስተያየት ሰጪዎች ቦርዱ የሰራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ የወሰደውን ፈጣን የአስተዳደር እርምጃ አድንቀዋል።
በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ባሉበት ሆነው አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግላቸውና አስፈላጊ ከሆነም አነስተኛ ስብሰባዎች በጤና ሚኒስቴር እውቅና እና ክትትል ሊደገፉ እንደሚገባም መግለጻቸው ይታወቃል።