የዶ/ር አብይ የጸረ ኮሮና ቁሶችን ማካፍል ፣የሙከራ ክትባቱ..|| ታምሩ ገዳ

የዶ/ር አብይ የጸረ ኮሮና ቁሶችን ማካፍል ፣የሙከራ ክትባቱ..|| ታምሩ ገዳ

የኢትዮጵያው ጠ/ሚ/ር ዶክተር አብይ አህመድ ለኢትዬጵያ እና ለአፍሪካ አገራት የጸረ ኮሮና ቫይረስ ዘመቻ የሚውል የህክምና ነክ ቁሳቁስ እርዳታ ከቻይናዊው ቱጃር ማግኘታቸውን ገለጹ።

ዶ/ር አብይ አህመድ በትላንትናው እሁድ፣ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ለሁሉም የአፍሪካ አገራት የሚከፋፈል የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ የሚሆን መሳሪያዎች፣ አፍንጫን መሸፈኛ ጭንብሎች (ማስክስ) እና ሰለቫይረሱ ምንነት የሚገልጹ፣ መመሪያ የሚሰጡ መጻህፍቶችን ከአለማችን ቱጃሮች መካከል አንዱ ከሆኑት ፣ከጃክ ማኣ አንደተቸራቸው የገለጹ ሲሆን እንደ ዶ/ር አብይ ገለጻ እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ከአስር ሺህ እስከ ሃያ ሺህ የምርመራ ቁስ (test kits) ያገኛል።

የአፍንጫ መሸፈኛ፣ ጭንብል፣ በተመለከተም እያንዳንዱ አገር ወደ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጋ ማስክ በነፍስ ወክፍ ያገኛል። የሃምሳ አምሰት አመቱ ቻይናዊው የአሊባባ ኩባንያ መስራች ጃክ የአርባ ቢሊዮን ዶላር ባለጸጋ ሲሆኑ በጸረ ኮሮና ዘመቻ ላይ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በቅርቡ ለአሜሪካ አስተዳደር የአንድ መቶ ሚሊዬን ጭምብል እና የግማሽ ሚሊዮን የመመርመሪያ ቁስ (Test kits) እንደሚለግሱ የገለጹ ሲሆን ጃፓን፣ ኢራን፣ ጣሊያን ስፔን የመሳሰሉት አገራትም ተመሳሳይ እርዳታ እንደሚያገኙ ቱጃሩ ጃክ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ በሽታዎች ላይ ለሚደረገው ሳይንሳዊ ምርምር የሚውል የአስራ አራት ሚሉዮን ዶላር ልገሳ እንደሚያደርጉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።

ባለፈው ጥር/ጀነዋሪ 17,2020 እኤአ በቻይና ውስጥ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሃያ አራት የአፍሪካ አገራት፣ በተጨማሪ ሰማኒያ የሚጠጉ የአለም አገራት ውስጥ አንድ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ሰዎችን ለክፏል፣ ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ቀጥፏል ።

ይህ በዚህ እንዳለ እስከ አሁን ድረስ የመከላከያ ክትባት መድሃኒት ያልተገኘለት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመመከት በአሜሪካ ዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ውስጥ የሚገኘው የካይዘር ፐርመነንቴ (Kaiser permanente) ሆስፒታል የምርምር ማእከል ዛሬ ሰኞ በአራት ፍቃደኛ ሰዎች ላይ የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ የክትባት ሙከራ አድርጓል።

ለሙከራ ክትባቱ ሲሉ የመጡት የአርባ ሶስት አመቷ ጀኒፈር ሄይለር ከሆስፒታሉ ስወጡ “ውስጤ በሐሴት ተሞልቷል፣ የዚህ ታሪካዊ ሙከራ ተሳታፉ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል በፈገግታ። አርባ አምስት ፍቃደኛ ሰዎች የሚቀላቀሉት ሙከራው ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ እና ወደ ተግባር ለመግባት ቢሮክራሲያዊ ውጣውረዶችን ማለፉ ግድ ነው ተብሏል

የምርምር ማእከሉ የቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ሊዛ ጃክሰን “ሁሉም ሰው በዚህ ቀውጢ ወቅት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ፍቃደኝነታቸውን አሳይተውናል “ብለዋል።

LEAVE A REPLY