በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ በኮሮና የተጠቁ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንና ዘጠኝ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሜኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገለጹ።

በአገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው የመጀመሪያ ግለሰብ የዛሬ ሳምንት መጋቢት 04/2012 ዓ.ም ይፋ ከተደረገ በኋላ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር አሁን ዘጠኝ ደርሷል ቢባልም ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል በመነገር ላይ ነው።

በሽታው ከተገኘባቸው ከአዲሶቹ ሦስት ሰዎች መካከል አንደኛው የ44 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ጃፓናዊ፣ ሌላው የ39 ዓመት ኦስትሪያዊ፣ እንዲሁም ሦስተኛዋ የ85 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ኢትዮጵያዊት መሆናቸው ታውቋል። አዲስ በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡት ሦስት ሰዎች ውስጥ ጃፓናዊው ግለሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠው ጃፓናዊ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲኾኑ፣ የ85 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ደግሞ ከሁለት ሳምንት በፊት ከውጪ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው።

ዘጠነኛው በበሽታው መያዙ የተረጋገጠው ግለሰብ ደግሞ ኦስትሪያዊ ዜግነት ያለው ሲሆን ከቀናት በፊት ከስዊትዘርላንድ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ተገልጿል። ግለሰቡ እራሱን ለይቶ ካቆየ በኋላ የበሽታው ምልክቶች ስለታየበት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገባ መደረጉንና በተደረገለት ምርመራ ቫይረሱ ሊገኝበት መቻሉ ተገልጿል።

እስካሁን በሽታው እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች አራቱ ጃፓናዊያን፣ ሶስቱ ኢትዮጵያዊያን፣ አንዷ እንግሊዛዊት እና አንዱ ኦስትሪያዊ ናቸው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳመለከተው ቀደም ሲል በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ በህክምና ላይ ከሚገኙት ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ ከበሽታው ማገገማቸውን ሁለቱ ድግሞ እያገገሙ እንደሆነ አመልክቷል።  በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 250,000 የደረሰ ሲሆን የሞቱት ደግሞ 9,900 መሆናቸው ተነግሯል።

LEAVE A REPLY