ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከቤት ውጪ የሚደረጉ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በገደበችው አውስትራሊያ ፖሊስ ሲድኒ ከተማ ቦንዲ የባህር ዳርቻ ‘ስለ ኮሮናቫይረስ አልሰማንም አላየንም’ በሚመስል መልኩ ሲዝናኑ የነበሩ ሰዎችን በመበተን የባህር ዳር መዝናኛውን ዘጋ።
አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከጣለቻቸው እገዳዎች መካከል በሃገሪቱ የሚያደረጉትን ስብሰባዎችን ማገድ ነው።
ነገር ግን በርካታ ሰዎች ለመዝናናት በሲድኒ ወደ ሚገኙ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎች እየተመሙ መሆኑ እየተነገረ ነው።
በእነዚህ የባህር ዳር መዝናኛዎች ብዙዎች ዓለም ላይ ምንም ስጋት እንደሌለ በሚመስል መንፈስ ሲዝናኑ የሚያሳዩ ፎቶዎች ትናንት በመገናኛ ብዙሃን፤ በማህበራዊ ሚዲያም ሲዘዋወር ውሏል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ግሪግ ሀንት የባህር ዳር ተዝናኞቹ ባህሪ ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
የሚመለከታቸው ህግ አስከባሪ አካላት ማህበራዊ ርቀት መጠበቅን በሚመለከት የተቀመጠው ነገር ተግባራዊነትን ለማረጋገጥ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
አውስትራሊያ ባስቀመጠችው እገዳ መሰረት ዜጓቿ በማንኛውም ቦታ ላይ አንዳቸው ከአንዳቸው አንድ ሜትር ተኩል መራቅ አለባቸው።
በሌሎች ተመሳሳይ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎች ተመሳሳይ ነገር የሚታይ ከሆነ ርምጃ እንደሚወሰድ መንግሥት አስታውቋል።
እንደ መጠጥ ቤት እና ሬስቶራንት ባሉም በአራት ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ከአንድ ሰው በላይ እንዳይገኝ አግዳለች አውስትራሊያ።
ነገር ግን አሁንም በአንድ ጣሪያ ስር 100 ሰዎች ከቤት ውጭ ደግሞ 500 ሰዎች አንድ ላይ መገኘት የሚችሉ ሲሆን ከዚህ ውጭ የሚሆን ቁጥር ህገወጥ ነው።