የአተየቸየአበባ አምራቾች ለሰራተኛ ደመወዝ መክፈል እንደተቸገሩ አሳስበዋል

የአተየቸየአበባ አምራቾች ለሰራተኛ ደመወዝ መክፈል እንደተቸገሩ አሳስበዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ በሆነው ኮሮናቫይረስ ምክንያት በጥቂት ቀናት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ማጣታቸውን የአበባ አምራቾች ገለጹ።

ኢትዮ አግሪሴፍት በሆለታ እና በባህርዳር ካሉት ሁለት የአበባ እርሻዎች በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን አበባ ዘንግ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ያቀርብ እንደነበር ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ኢሳያስ ከበደ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ በቀጥታ እና በጨረታ ለዓለም ገበያ በሽያጭ ይቀርብ የነበረው አበባ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ ወርዷል።

በየቀኑ እስከ 45ሺህ ዘንግ የሚጠጋ አበባ ለዓለም ገበያ ያቀርብ የነበረው አግሪ ሴፍት ከማርች 15 በኋላ በመቋረጡ በየቀኑ 21200 የአሜሪካ ዶላር ወይም 678400 ብር እያጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ድርጅቱ ሠራተኞቹን እረፍት እንዲወጡ እያደረገ ከመሆኑም በላይ በየቀኑ ወደ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጋ የአበባ ዘንግ ወደ ኮምፖስተነት ለመቀየር ተገዷል።

ከባህርዳር ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው ጣና ፍሎራም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተመሳሳይ ችግር ገጥሞታል።ድርጅቱ ባለፉት ስምንት ቀናት ብቻ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዘንግ ገበያ በማጣት ምክንያት ለመጣል መገደዱን የጣና ፍሎራ ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት በላይነህ ገልጸዋል።

ባለፉት ስምንት ቀናት በገጠመው የገበያ ችግር ምክንያት ወደ 10 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማጣቱን አስታውቀዋል። አክለውም ከ700 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞቹም ያለሥራ መቀመጣቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አበባና አትክልት አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር በተለይ ለቢቢሲ እንደገለጹት ማህበሩ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጀምሮ በሥራቸው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተጽዕኖ እና በእርሻዎቹ እንዳይሰራጭ ለማድረግ እየተሠራ ቆይቷል።

ከየካቲት እስከ ግንቦት ያሉት ወራት በአበባ ሥራ ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት መሆኑን ጠቅሰው አሁን ያለው የአበባ ዋጋ ካለፈው አመት አማካይ ጋር ሲነጻጸር በ85 በመቶ መቀነሱን አስታውቀዋል።

በቶሎ የሚበላሽ እና የማይከማች ምርት ከመሆኑም በላይ የወጪ ንግዱ 80 በመቶ ቅናሽ በማሳየቱ አምራቾችን በገንዘብ ረገድ እንዲፈተኑ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ ከሆነ በአሁኑ ወቅት አበቦች እንዳይጎዱ በመንከባከብ እና ቀሪ ሠራተኞችን ደግሞ እረፍት እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከስምንት መቶ በላይ ሠራተኞች ያሉት ድርጅቱ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ደሞዝ ለመክፈል እንደሚቸገር ተናግረዋል። በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት አቶ አብነት በበኩላቸው መንግስት በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ችግሩ ከመባባሱ በፊት መንግስት ድርጅቶች ብድር የሚከፈሉበትን ጊዜ በማስረዘም፤ ተጨማሪ ብድር የሚያገኙበትና የአበባ ፍላጎት ወዳሉባቸው አገራት ካርጎ እንዲጀመር የኢትዮጵያ አበባና አትክልት አምራች ላኪዎች ማህበር ጠይቋል።

መንግስት ችግሩን መገንዘቡንና በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ምላሽ ይሰጣል ብለው እንደሚጠብቁ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጨባጭ ጉዳት ፈጥኖ በመለየት የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ መንግሥት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መግለፃቸው ይታወሳል።

LEAVE A REPLY