ፀደይን በመስኮት || በእውቀቱ ስዩም

ፀደይን በመስኮት || በእውቀቱ ስዩም

 

ክረምቱ ሲወጣ
ርጥብ ዳሱን ነቅሎ
አዳሜ
ከተሜ
ጃንጣላውን ሰቅሎ
ካቦርታውን ጥሎ

አዳም ከሄዋኑ
(ድስት ከነክዳኑ)
ላጤውም ለብቻው
ወንዱ ደረት ሊያሳይ
በባህር ዳርቻው
ሴቱም እንደልቡ፤ ቂጡን እየጣለ
በሙቅ አሸዋ ላይ
እየተንጋለለ
ቅብጠት ድርያ፤ ሲያምረው፤
ማጭድ ታጥቆ ገባ
ሁሉን የማይምረው፤
ፊት ያለውን ሁሉ
በብረት መዳፉ፤ የሚያጠናግረው ፤

እምቢልታ ተነፋ
ደወል ተደወለ
ያልታደለው ጠፋ
ቀሪው እቤት ዋለ
ሰው ቤቱ መሸገ
መስኮት እንደጋሻ፤ አየወለወለ፤

በየአደባባዩ
እዩኝ እዩኝ ባዩ
እንዳልተጀነነ
ሰው ለመኖር ብሎ፤ ከኑሮ መነነ!

እኔም እንዳገሬው፤ ለነፍሴ ብሳሳ
ለብሻት ሰነበትኩ፤ ቤቴን እንደገሳ፤

አምና እንዳልነበርኩኝ
የተፈጥሮ ሚዜ፤ የፀጋው ተካፋይ
የእልፍኝ እስረኛ ነኝ ፤ አጮልቄ የማይ
ያውና እዚያ ማዶ፤ጥርት ያለ ሰማይ
ያቻት እዚያ ማዶ፤ ያልተሞቀች ፀሀይ!

በየልምላሜው
በየዛፍ ቅጠሉ
ንቡ ወፉ ትሉ
ሲቦርቅ ሲራኮት!
እኔ ግን ሸኘሁት! ፀደይን በመስኮት፤

LEAVE A REPLY