በኮረና የተያዙት ሁለት ሰዎች የተገኙት በአማራ ክልል ውስጥ መሆኑ ታወቀ፤ ቅላላ 23...

በኮረና የተያዙት ሁለት ሰዎች የተገኙት በአማራ ክልል ውስጥ መሆኑ ታወቀ፤ ቅላላ 23 ደርሷል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኮሮናቫይረስ መያዘቸው በዛሬው ዕለት የተገለጹት ሁለት ሰዎች የተገኙት በአማራ ክልል ውስጥ እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የህሙማኑ ቁጥር 23 መደረሱን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንን ተከትሎ በወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ሁለቱ ግለሰቦች የቅርብ ጊዜ የውጪ አገር ጉዞ ታሪክ የነበራቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል።

አንደኛዋ በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴት መጋቢት 10 ላይ ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን ሌላኛው 32 ዓመት ወንድ ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ነዋሪና መጋቢት 12 ቀን ከአሜሪካ የመጣ ጎልማሳ መሆኑ ተገልጿል።

ሁለቱም ግለሰቦች የበሽታው ምልክቶች ስለታዩባቸው ምርመራ ተደርጎባቸው ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋገጦ በክልሉ የለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከግለሰቦቹ ጋር የቅርብ ንክኪ አላቸው የሚባሉ ሰዎችን የመከታተልና የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ባለፉት ሦስት ሳምንታ ውስጥ ከውጭ አገራት ወደ ክልሉ የገቡ ዜጎች በየአካባቢያቸው ወደ ሚገኙ የመንግሥት የጤና ተቋማት በመቅረብ ሪፖርት እንዲያደርጉ አዘዘ።

በክልሉ የገጠር አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችም የተከሰተው ወረርሽኝ አስቸጋሪ መሆኑን በመረዳት ለግብይትም ሆነ ለሌላ ማኅበራዊ ጉዳዮች ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ በማቆም ባሉበት ሆነው ራሳቸውን እንዲጠብቁም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በተጨማሪም የክልሉ ነዋሪዎች አሁን ካለው የወረርሽኙ አሣሣቢነት አንፃር እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ በክልሉ ውስጥ የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊቋረጥ ስለሚችል፤ ይኸንኑ በመረዳት በቋሚ የመኖሪያ ቦታቸው ላይ በመሆን ከመንግሥት የሚሠጠውን ትዕዛዝ እንዲጠባበቁ ኮሚቴው አሳስቧል።

LEAVE A REPLY