|| ለመድረስ የፌስቡክ ጓደኞች ቅብብልን ታሳቢ ያደረገ የተማፅኖ ደብዳቤ ||
ክብርት ሆይ!!
ሰላም ለርስዎ ይሁን!! ከወቅቱ አለም-ዳሰስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ባፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀላቸው ሁኔታውን የሚያባብሱ፤ በርስዎ እና በሾመዎት መንግስት መስተካከል የሚችሉ፤ የጤና ባለሙያዎችን የተመለከቱ ጥቂት ነጥቦች ላሣሥብዎ ወደድኩ።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጀምሮ እስከ መቆጣጠር ድረስ ላለው ሂደት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የጤና ባለሙያዎች መሆናቸው ሌጣ ሀቅ ነው። የጤና ባለሙያዎች ደግሞ ይህንን ኃላፊነት ሙያቸው በሚያስገድዳቸውና ዕውቀታቸው በፈቀደ ልክ ለመወጣት እነርሱ ጤነኛ መሆን ይገባቸዋል።
ለዚህ ምክንያቱ የነርሱ የጤና ዕክል፤ መስጠት ከሚገባቸው አገልግሎት ስለሚያግዳቸው ብቻ ሳይሆን ከህሙማን እና ከጤነኛው ወገን ጋር ያላቸው ተደጋጋሚ ንክኪ ከፍተኛ ስለሆነም ነው። በዚህም በሽታውን ተለይቶ ከሚታከመውም ሆነ ሳይታወቅ የቫይረሱ ተሸካሚ ሆኖ በሌላ ህመም አልያም ባስታማሚነት ወደ ጤና ተቋም ከመጣ ሰው ተቀብለው ወደ ጤነኛው ማህበረሰብ በቀላሉ ለማቀበል የሠፋ ዕድል አላቸው።
ጠባቂውን መጠበቅ ካልተቻለ ጥበቃ ሊኖር አይችልም!! ለዚህ በኔ ዕይታ ሁለት ነገሮች የወሠዱትን ወስደው አጣዳፊ መፍትሔ ይፈልጋሉ። አንደኛው የግል ደኅንነት መጠበቂያ ቁሳቁስን ማሟላት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቂ የትራንስፖርት አቅርቦት ነው ።
ክብርት ሆይ!!
ሁለቱም ጉዳዮች “አቅጣጫ ማሥቀመጥ” ና “ኮሚቴ ማዋቀር” የሚሉ ጊዜ በል ቅድመ-ሁኔታዎችን ወደ ጎን በመተው በአፋጣኝ ወደ ድርጊት መግባትን ይጠይቃሉ።
የግል ደኅንነት መጠበቂያዎችን በተመለከተ ከውጭ ገበያ አቅርቦት እስኪገኝ ድረስ በአገር ውስጥ ከፍተኛ ክምችት ካለባቸው ዕጥረት ወዳለባቸው በማንቀሳቀስ ክፍተትን ለመድፈን መሞከር ይቻላል።
በተጨማሪም ተቀራራቢ ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ትኩረት ሰጥተው ባጭር ጊዜ አስፈላጊ ቁሶችን እንዲያመርቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም ያስፈልጋል።
(ለምሳሌ :- የጨርቃጨርቅ አምራቾችን የፊት መከለያ ጭንብል MASK እንዲሸምኑ፤ የፕላስቲክ ውጤት ፈብራኪዎች ደግሞ ሙሉሠውነት የሚሸፍኑ አልባሳትን እንዲሠሩ፤ ሌሎችም የአይን መከለያ መነፅር፣ ሄልሜት፣ ጓንት እና የመሣሠሉትን እንዲያዘጋጁ ማግባባት ካልሆነም ማስገደድ።)
ለግዳጁ አጣዳፊ የማህበረሰብ ጤና ዕክል (public health emergency ) እንደምክንያት ማቅረብ እና በህግ መደገፍ ይቻላል።
ለባለሙያዎች የተለዩ መጓጓዣዎችን በተመለከተ የመንግስት፣ የበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማስተባበር በቀላሉ ማመቻቸት ይቻላል።
ይህ ካልሆነና አሁን በስፋት እንደሚታየው የጤና ባለሙያዎች ከሌላው ነዋሪ ጋር ትከሻ እየተለካኩ በንግድ መኪኖች መጠቀማቸውን ከቀጠሉ የሚከሠተው አደጋ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍን ያህል እንኳ የቀለለ አይሆንም።
ክብርት ሆይ!!
ለነዚህ ሁኔታዎች እጅግ በጣም ፈጣን መፍትሔ ካላበጀን ወቅቱ የሚጠይቀውን አዳኝ ባለሙያ ሳይሆን አጥፍቶ ጠፊ ሀኪሞችን እንደምንፈጥር ሳናልም የምንፈታው ጉዳይ ነው።
ተከላካዮች በራስ ግብ ላይ የሚዘምቱ አጥቂዎች እንዳይሆኑ እኔ ያቀረብኩት መላ የሞኝ ነው ብለው ካሰቡ እንኳ የተሻለ መላ ባስቸኳይ ዘይደው እልባት እንዲያበጁ እማፀንዎታለሁ።
ለጤናችን በጋራ እንሰራ!!!
አክባሪዎ!!